ቀጥታ፡

የዳበረ የሲቪል ምዝገባ ስርዓት የጤናና ትምህርት አገልግሎቶችን በማረጋገጥ ዘላቂ የልማት ግቦችን ማሳካት ያስችላል 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 1/2018 (ኢዜአ)፡-የዳበረና የተደራጀ የሲቪል ምዝገባ ስርዓት የጤናና ትምህርት አገልግሎቶችን በማረጋገጥ የ2030 ዘላቂ ልማት ግቦችን ማሳካት እንደሚያስችል የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሰሀረላ አብዱላሂ ገለጹ።

ስምንተኛው የሲቪል ምዝገባና ቫይታል ስታቲስቲክስ ቀን "የሲቪል ምዝገባ ለህብረተሰቡ የዲጂታል መሰረተ ልማትና ህጋዊ ማንነት ስርዓት መሰረት ነው" በሚል መሪ ሀሳብ እየተከበረ ነው።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሰሀረላ አብዱላሂ በዚህ ወቅት እንዳሉት፣ የዳበረና በአግባቡ የተደራጀ የሲቪል ምዝገባ ስርዓት ልደትና ሞትን ጨምሮ የወሳኝ ኩነቶችን ምዝገባ ያረጋግጣል።

ለዚህም ዜጎች ለምዝገባ ማረጋገጫ አስፈላጊ የሆኑ የምስክር ወረቀት እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል።


 

ከሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ ስርዓት የሚገኝ መረጃ ለአንድ ሀገር ልማት፣ ለፖሊሲና ስትራቴጂ ቀረፃ እንዲሁም ለተሟላ የዕቅድ ዝግጅት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

የ2030 ዘላቂ የልማት ግቦችን ዕውን ለማድረግ የተጀመረው ጥረት የበለጠ ትክክለኛ እንዲሆን ያደርጋል ብለዋል።

የወሳኝ ኩነት ምዝገባና ቫይታል ስታቲስቲክስ ስርዓት የአንድ ግለሰብ ከመንግሥት ጋር ለሚኖረው ግንኙነት የሰነድ ማስረጃ ሆኖ የሚያገለግል መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ጤናና ትምህርት ያሉ መሰረታዊና አስፈላጊ አገልግሎቶችን ለማግኘትና የንብረት ባለቤትነትን ለማረጋገጥ ያስችላል ብለዋል።

ከ17ቱ ዘላቂ የልማት ግቦች 12ቱ፤  ከ232 የዘላቂ ልማት ግቦች አመላካቾች መካከል 67 በወሳኝ ኩነቶች መረጃ ላይ የተመረኮዙ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ መረጃው የእናቶችና ጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስና ድህነትን ለማስወገድ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

ስለሆነም አካታችና ቀጣይነት ያለው ሆኖ ምዝገባው በህግ ተደግፎ ተግባራዊ መሆኑን ገልጸዋል።

በአዋጁ በጤና ተቋምና ከጤና ተቋም ውጭ የሚከሰቱ የልደትና የሞት ኩነቶችና የሞት ምክንያት የሚያሳውቁ የጤና ባለሙያዎች በመላ ሀገሪቷ እንዲሰማሩ መደረጉን ገልጸዋል።

በዚህም የልደትና የሞት ኩነትና የሞት ምክንያት ማሳወቂያ መስጠት ከተጀመረበት 2010 ዓ.ም አጋማሽ ወዲህ በየዓመቱ እድገት በማሳየት በ2017 በጀት ዓመት መጨረሻ በሀገራችን በህይወት ከተወለዱ ህፃናት መካከል 82 በመቶ ማሳወቂያ መሰጠቱን ገልጸው፤ ከሞት አኳያ የተሰጠው ማሳወቂያ ከአምስት በመቶ በታች መሆኑን ተናግረዋል።

እነዚህን ክፍተቶች በማረም የተሻለ የሲቪል ምዝገባ ስርዓት ለማከናወን ሁላችንም በትብብርና በትኩረት መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም