ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ባህላዊ ምግቦች ለዓለም ማስተዋወቅና ለአዳዲስ የኢኮኖሚ ሃብት መፍጠሪያነት ማዋል ያስፈልጋል -ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 1/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ባህላዊ ምግቦች ለዓለም ማስተዋወቅና ለአዳዲስ የኢኮኖሚ ሃብት መፍጠሪያነት መጠቀም እንደሚያስፈልግ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።

በቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩትና ኩሪፍቱ ሪዞርት የአፍሪካ መንደር ትብብር የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግቦች ፌስቲቫል መካሄድ ጀምሯል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በዚህ ወቅት፥ ፌስቲቫሉ የኢትዮጵያውያንን ባህላዊ ምግብና መጠጦች ለማስተዋወቅ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ነው ብለዋል።

በክህሎት ልማትና በሥራ ዕድል ፈጠራ የኢትዮጵያን የብልጽግና ተምሳሌትነት የሚያረጋግጡ ወሳኝ ስኬቶች እየተመዘገቡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያውያን ባህላዊ ምግቦች በርካታ አዳዲስ የኢኮኖሚ ሃብት መፍጠር የሚችሉ እሴቶች መሆናቸውን አንስተዋል።

ባህላዊ ምግቦቻችን የኢትዮጵያን መልከብዙነት የሚገልጡ የህብረ ብሔራዊነታችን እሴቶች ናቸው ያሉት ሚኒስትሯ፥ እነዚህን ሃብቶች በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ የገቢ ምንጭና የስራ ዕድል መፍጠሪያ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።


 

የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነጋሽ፥ ኢትዮጵያ በዘላቂነት ከቱሪዝም ተጠቃሚ መሆን የምትችልባቸው ጸጋዎች ባለቤት ናት ብለዋል።

ኢንስቲትዩቱ የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግብና መጠጦች ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ እንዲተዋወቁ የጥናትና ምርምር እንዲሁም ሙያዊ የማማከር ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም በጥናት የተለዩ የኢትዮጵያውያን ባህላዊ ምግብና መጠጦች በኩሪፍቱ አፍሪካ ቪሌጅ መቅረባቸውን ገልጸዋል።

የኩሪፍቱ ሪዞርቶች ባለቤት አቶ ታድዮስ ጌታቸው÷ የኩሪፍቱ አፍሪካ መንደር የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግቦችን ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ እያስተዋወቀ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በፌስቲቫሉ ላይ ከሁሉም ክልሎች ለማሳያነት የተመረጡ የብሔር ብሔረሰቦች ባህላዊ ምግቦች ቀርበዋል።

ፌስቲቫሉ ባህላዊ ምግቦችን በማስተዋወቅ ወደ ገበታ እንዲመጡ ማድረግ፣ የእርስ በርስ ትውውቅን መፍጠር፣ የሀገር ገጽታ መገንባትና የምግብ ቱሪዝምን ለማሳደግ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም