ቀጥታ፡

ሰንደቅ ዓላማችን  የክብራችንና የማንነታችን ማህተም  በመሆኑ ልዩ ክብር ልንሰጠው ይገባል - አፈ-ጉባኤ መሠረት ማቲዎስ

ጋምቤላ ፤ ጥቅምት 1/ 2018(ኢዜአ)  ሰንደቅ ዓላማችን  የትናንት የጋራ ታሪካችን፣ የዛሬ የጋራ ጥረታችንና የነገ ተስፋችንን አጣምሮ የያዘ የክብራችንና የማንነታችን ማህተም ነው ሲሉ የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ መሠረት ማቲዎስ ገለጹ። 

18ኛው ብሔራዊ  የሰንደቅ ዓላማ ቀን አካባበርን አስመልክቶ የተዘጋጀ የፓናል ውይይት ዛሬ በጋምቤላ ተካሄዷል። 


 

የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ መሠረት ማቲዎስ  በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር፤  ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ የትናንት የጋራ ታሪካችን፣ የዛሬ የጋራ ጥረታችንና የነገ ተስፋችንን አጣምሮ የያዘ የክብራችንና የማንነታችን ማህተም በመሆኑ ልዩ ክብር ልንሰጠው ይገባል ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ህብረ ብሔራዊ አንድነትንና ዘላቂ መግባባትን የሚያጠናክር የጋራ ዓርማችን ነውም ብለዋል። 

ዕለቱ ቀደምት አባቶች ለሰንደቅ ዓላማው ክብርና ለሀገራቸው ሉዓላዊነት ሲሉ የከፈሉትን መስዋዕትነት የምንዘክርበት ጭምር መሆኑን ተናግረዋል። 

በዓሉን በየዓመቱ መከበሩ ዜጎች ስለ ሰንደቅ ዓላማው ክብርና ትርጓሜ በተገቢው መንገድ ግንዛቤ እንዲኖራቸው እድል የሚፈጥር ነው ብለዋል። 

የሰንደቅ ዓላማ ቀንን ስናከብር ቀደምት አባት አያቶቻችን ሉዓላዊነቷንና ክብሯን ጠብቀው ያስረከቡንን አንድነቷ የተጠበቀና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስረከብ ቃላችንን የምናድስበት ዕለት ነው ብለዋል። 

ከፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ቾል ኮር በሰጡት አስተያየት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ የሁላችንም የማንነት መገለጫ በመሆኑ ልዩ ክብር እንሰጠዋለን ብለዋል። 


 

ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማችን ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባትና የህዝቦችን አንድነትና አብሮነት ለማጠናከር የሚያስችል ነው  ያሉት ደግሞ ፓስተር ማን ሙን ናቸው ። 


 

ቄስ ልብሰ ወርቅ በበኩላቸው ሰንደቅ ዓላማው ኢትዮጵያዊ አንድነታችን የሚጠናከርበትና ማንነታችን በዓለም መድረክ ጎልቶ እንዲተዋወቅ የሚያደርግ ዓርማ ነው ብለዋል። 


 

በፓናሉ ላይም ስለ ሰንደቅ ዓላማ ትርጓሜ የሚዳስስ ጽሁፍ ቀርቦ በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎበታል።

የሰንደቅ አላማ ቀን ''ሰንደቅ ዓላማችን ለኢትዮጵያ ታላቅ የከፍታ ዘመን ብስራት ፤ ለብሔራዊ አንድነታችን ፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ህዳሴ'' በሚል መሪ ሀሳብ የፊታችን ሰኞ ጥቅምት 03/2018 ቀን በሃገር አቀፍ ደረጃ እንደሚከበር ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም