የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ ዘመናዊነትን የተላበሰ ማህበረሰብ ለመፍጠርና የበለፀገች ሀገር ለመገንባት ወሳኝ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ ዘመናዊነትን የተላበሰ ማህበረሰብ ለመፍጠርና የበለፀገች ሀገር ለመገንባት ወሳኝ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 1/2018(ኢዜአ)፦ የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ ዘመናዊነትን የተላበሰ ማህበረሰብ ለመፍጠርና የበለፀገች ሀገር ለመገንባት ወሳኝ መሆኑን የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት ገለጹ።
ስምንተኛው የሲቪል ምዝገባ እና ቫይታል ስታቲስቲክስ ቀን "የሲቪል ምዝገባ ለህብረተሰቡ የዲጂታል መሰረተ ልማትና ሕጋዊ ማንነት ሥርዓት መሰረት ነው" በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ነው።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በአዋጅ ቁጥር 1370/2017 መሰረት ከፌደራል እስከ ታችኛው የአስተዳደር እርከን ድረስ ራሱን የቻለ አደረጃጀት ያለው ሆኖ የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ የማከናወን፣ የመምራት፣ የማስተባበር፣ የመደገፍ፣ የምዝገባ መረጃዎችን የማስተዳደርና የማደራጀት፣ በብሔራዊ ደረጃ በመረጃ ቋት አደራጅቶ የመያዝ ኃላፊነት ተሰጥቶታል።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት እንደገለጹት፤ የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ ዘመናዊነትን የተላበሰ ማህበረሰብና የበለጸገች ሀገር ለመፍጠር ወሳኝ ነው።
የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ ውጤታማ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የልደት፣ ጋብቻና ሞት የወሳኝ ኩነት አገልግሎቶች ምዝገባ መከናወን ከጀመረ ረጅም ዓመታት ቢቆጠሩም፣ በሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ የተደራጀ ባለመሆኑ ከምዝገባ የሚመነጨው ውጤት እዚህ ግባ የሚባል ሀገራዊ ጥቅም ሳይሰጥ ቆይቷል ብለዋል።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በኢትዮጵያ ፈጣን ዕድገት ልክ ዘመናዊ የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ ስርዓት በማንበር የዘርፉን ችግሮች ለመፍታት በርካታ ሥራዎች እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
አገልግሎቱ የምዝገባ ስርዓቱን ዲጂታላይዝ በማድረግና ምዝገባውን በማዘመን የተማከለ የመረጃ አሰባሰብና አስተዳደር ስርዓት እየዘረጋ ነው ብለዋል።
ከኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት አዲስ መተግበሪያ በማበልጸግ ከፌደራል እስከ ቀበሌ ከብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ፣ ከፓስፖርት እና መሰል መረጃዎች ጋር የተቀናጀ ዲጂታል የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ ስርዓት ገቢራዊ ማድረግ የሚያስችል አቅም ተገንብቷል ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ ካሉ 19ሺህ በላይ ቀበሌዎች መካከል በ6ሺህ 200ዎቹ የዲጂታል የምዝገባ ስርዓት ሙከራ መጀመር የሚያስችል የሰው ኃይል፣ የቴክኖሎጂ እና የአደረጃጀት ስርዓት መፈጠሩንም ገልጸዋል።
የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ ስርዓትን በዲጂታል ማድረግ አንድ ሰው አንድ ማንነት ኖሮት አገልግሎትን ከማቀላጠፍ በላይ ብሔራዊ ደህንነትን ለማስጠበቅና ወንጀልን ለመከላከል የጎላ አብርክቶ አለው ብለዋል።
የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባን በተመለከተ የማህበረሰቡ ግንዛቤ አናሳ መሆን፣ የአመራሩ ቁርጠኝነት ማነስና በቀበሌዎች የግብዓት ውስንነት የዘርፉ ፈተናዎች መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ለመፍትሔው ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን በመቀመር ከአጋር አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የተመዘገቡ የሲቪልና ቤተሰብ መረጃዎችን ወደ ስታቲስቲክስ መረጃ በመለወጥ ለተጠቃሚዎች ተደራሽ እንደሚደረጉ ተናግረዋል።
አገልግሎቱ ተዓማኒና ጥራት ያለው የስታቲስቲክስ መረጃ ለተጠቃሚዎች ለማድረስ በአጋርነት እየሰራ መሆኑን ገልጸው፣ ትብብራችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ የዘመናዊና ስልጡን ማህበረሰብ መገለጫ መሆኑን በመጥቀስ፤ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ልማትን ለማቀድና የዜጎችን አገልግሎት ለማሳለጥ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
ሀገራዊ የ10 ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ የዘላቂ የልማት ግቦችን ስኬት ለመለካት ወሳኝ የመረጃ ምንጭ ሆኖ እንደሚያገለግልም ገልጸዋል።
የምዝገባ ስርዓቱ በዲጂታል አሰራር ታግዞ ከሀገራዊ እድገት ጋር የሚራመድ መሆን አለበትም ነው ያሉት።