ቀጥታ፡

ሰንደቅ ዓላማችን  የሃገራችንን ክብርና ልዕልና የምናስቀጥልበት  የነጻነታችን መገለጫ ምልክታችን ነው 

ሰቆጣ/ ደሴ፤  ጥቅምት 1/2018(ኢዜአ)፡-  ሰንደቅ ዓላማችን የሃገራችንን ክብርና ልዕልና የምናስቀጥልበት፣ የሉዓላዊነታችንና የነጻነታችን መገለጫ የጋራ ምልክታችን ነው ሲሉ የሰቆጣና ደሴ ከተማ ነዋሪዎች  ገለጹ። 

ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን  ጥቅምት 3/2018 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ እንደሚከበር ይታወቃል። 

ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚመለክተው፤ የሰንደቅ ዓላም ቀን መከበሩ ለብሔራዊ አንድነት፣ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ከፍታ ብሎም ብሔራዊ መነቃቃት ለመፍጠር ትልቅ ትርጉም አለው። 

የሰንደቅ ዓላማ ቀንን በማስመልከት ኢዜአ በሰቆጣና ደሴ ከተሞች ነዋሪዎችን አነጋግሯል።  

ከሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች መካከል ሃጂ ካሳሁን ሁሴን በሰጡት አስተያየት፤ ሰንደቅ ዓላማችን የኢትዮጵያ መለያና የብሔራዊ ማንነት መገለጫችን ነው ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ለቅኝ ገዥዎች አልገዛም ባይነትን ያሳየንበት፤ ለመላው ጥቁር የነፃነትና የእኩልነት ተምሳሌት በመሆኑ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ማድረግ አለብን ብለዋል።

ቄስ አበራ ውቤ በበኩላቸው፤ ሰንደቅ ዓላማችን ኢትዮጵያውያን በአንድነትና በክብር ፀንተው በየጊዜው የሚገጥሟቸውን ችግሮች በጋራ እንዲፈቱ በማስተሳሰር የላቀ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።


 

ወጣቶችም የሰንደቅ ዓላማን ክብርና የሀገርን ታሪክ ይበልጥ በመረዳት ለብሔራዊ አንድነት መጠናከር በቁርጠኝነት መሰራት እንዳለባቸው አመልክተዋል።

''ሰንደቅ ዓላማችን ኢትዮጵያ በአለም መድረክ የምትገለጽበት የነፃነት ምልክት ነው'' ያሉት ደግሞ አቶ ሻምበል እንየው ናቸው።


 

ሃገራችን ከጥንት ጀምሮ ፀንታ፣ ታፍራና ተከብራ እንድትኖር ጀግኖች አባቶች ለሰንደቅ ዓላማዋ  ዋጋ ከፍለዋል ብለዋል።

ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ቸኮለ ተስፋው በበኩላቸው፤  በብዙ መስዋዕትነት ተከብሮ የኖረው ሰንደቅ ዓላማችን የሚታሰብበት ዕለት በህግ ተደንግጎ መከበሩ የሚበረታታ ነው ሲሉም ገልጸዋል። 


 

በተመሳሳይ ከደሴ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ሀሰን እሸቱ፤  ሰንደቅ ዓላማችን አባቶቻችን ለሀገራቸው ሉዓላዊነት፣ ነጻነትና ክብር ተዋድቀው ሀገርን  ያፀኑበት አኩሪ ምልክታችን ነው ብለዋል።


 

ሌላው የደሴ ከተማ ነዋሪ አቶ አብዱ መሀመድ በበኩላቸው፣ ሰንደቅ ዓላማችን የሀገራዊ ክብራችን፣ ሉዓላዊነታችንና የነጻነታችን መገለጫ በመሆኑ ለሰንደቅ ዓላማችን ልዩ ፍቅር እና ክብር አለን ነው ያሉት።


 

የሰንደቅ ዓላማውን ክብር፣ በማስቀጠል ታሪኩን  ለልጆቻችን እናወርሳለን ብለዋል።

''ሰንደቅ ዓላማችን ሀገራችን፣ ውበታችን፣ አንድነታችን፣ ነጻነታችንና ክብራችን ነው'' ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ፀሐይነሽ ደምሴ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም