ቀጥታ፡

በግብርናው ዘርፍ የኢትዮጵያን ማንሰራራት ዕውን የሚያደርጉ ውጤታማ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው - ሚኒስትር አዲሱ አረጋ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 1/2018(ኢዜአ)፦ በግብርናው ዘርፍ የኢትዮጵያን ማንሰራራት ዕውን የሚያደርጉ ውጤታማ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ ገለጹ።

የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋን ጨምሮ የዘርፉ ከፍተኛ አመራሮች በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቀቤና ልዩ ወረዳ በክላስተር የለማ የበቆሎ እርሻን ተመልክተዋል።


 

በምልከታው የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለሰ መኮንን(ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ(ዶ/ር)፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የግብርና ቢሮ ኃላፊ ኡስማን ሱሩር እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ በዚሁ ወቅት፤ ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ የጀመረቻቸው ስራዎች ውጤት እያስገኙ ነው ብለዋል።

በምርት ዘመኑ በተለያዩ ሰብሎች ከለማው ማሳ ውስጥ ከ12 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በክላስተር መልማቱን ጠቁመዋል።

በግብርናው ዘርፍ እየተከናወኑ ያሉ ውጤታማ ተግባራት የኢትዮጵያን ማንሰራራት ዕውን የሚያደርጉ መሆናቸውንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

በቀቤና ልዩ ወረዳ በምርት ዘመኑ 12ሺህ 500 ሄክታር መሬት በበቆሎ የለማ ሲሆን በልዩ ወረዳው በዓመት አራት ጊዜ የግብርና ልማት እንደሚከናወን ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም