የኢትዮጵያ የባህላዊ ምግቦች ፌስቲቫል ለመጀመሪያ ጊዜ ሊካሄድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባህላዊ ምግቦች ፌስቲቫል ለመጀመሪያ ጊዜ ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 30/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባህላዊ ምግቦች ፌስቲቫል ነገ በሸገር ከተማ ይደረጋል።
የባህላዊ ምግብ ፌስቲቫሉ የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢኒስቲትዩት ከኩሪፍቱ አፍሪካ ቪሌጅ፣ ከሸገር ከተማ አስተዳደር እና ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ነው።
የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢኒስቲትዩት የህዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ አስቴር ተክሌ፥ የኢንስቲትዩቱ ባለሙያዎች በክልሎች በሚገኙ የተለያዩ ብሄር፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች የሚገኙ ባህላዊ ምግቦች ላይ ጥናት ማድረጉን ለኢዜአ ገልጸዋል።
የባህላዊ ምግቦቹ አዘገጃጀት፣ የምግቡ መጠን፣ የሚይዟቸው ንጥረ ነገሮች እና አጠቃላይ ሂደቱን ከሚያሳዩ እናቶች አንደበት በመስማት እና የተግባር ስራ በመመልከት ሰነድ መዘጋጀቱን አመልክተዋል።
ኢኒስቲትዩቱ 205 ገደማ የሚሆኑ ባህላዊ የምግብ አይነቶችን በመሰነድ በመጽሐፍ መልክ እያዘጋጀ መሆኑን ጠቁመዋል።
ጥናት ከተደረገባቸው መካከል ለማሳያነት የተመረጡ የ31 ብሄር ብሄረሰቦች ባህላዊ ምግቦች በምግብ ፌስቲቫሉ ላይ ይቀርባሉ ብለዋል።
ማሰልጠኛ ተቋሙ የባህላዊ ምግቦቹን ምንነት የሚገልጸውን ሰነድ ለየብሄረሰቦቹ ተወካዮች እንደሚያስረክብም ጠቁመዋል።
ፌስቲቫሉ የባህላዊ ምግቦቹን ማስተዋወቅ፣ ወደ ገበታ እንዲመጡ እና ለተጠቃሚ እንዲደርሱ ማድረግ፣ ባህሎችን የማስተዋወቅ፣ የእርስ በእርስ ትውውቅን መፍጠር፣ የሀገር ገጽታ መገንባት እና የምግብ ቱሪዝምን የማሳደግ ፋይዳዎች እንዳሉት ነው ወይዘሮ ተክሌ ያብራሩት።
የእናቶችን ሀገር በቀል እውቀት ወደ ቀጣዩ ትውልድ የማሻገር አላማ እንዳለውም ገልጸዋል።
ኢንስቲትዩቱ በመስኩ ሰፊ ጥናት አድርጎ ባህላዊ ምግቦች በትላልቅ ሆቴሎች የምግብ ዝርዝር (ሜኑ) ውስጥ እንዲካተቱ እያከናወነ ያለውን ስራ የሚያግዝ እንደሆነም ተናግረዋል።
በቀጣይ የባህላዊ ምግብ እና መጠጦች አውደ ርዕይ፣ የጥናትና ምርምር ግኝቶች ይፋ የሚደረጉባቸው መድረኮች እንዲሁም ሌሎች ተጓዳኝ መርሃ ግብሮች እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል።
ፌስቲቫሉ የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢኒስቲትዩት ከሰጡት ተልዕኮዎች አንዱ የሆነው የጥናት እና ምርምር ውጤቶችን ለህዝብ ተደራሽ የማድረግ ስራ አካል እንደሆነም ነው የጠቀሱት።
በቀጣይ ተቋሙ በትላልቅ ሆቴሎች ባህላዊ ምግቦችን የምግብ ዝርዝር (ሜኑ) ውስጥ የማከተት ስራ ማስፋት እና የማስተዋወቅ እንዲሁም ሰነዶችን የማዘጋጀት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
በባህላዊ ምግብ ፌስቲቫሉ ላይ ምግቡን ያዘጋጁ እናቶች፣ የየብሄረሰቦቹ ተወካዮች፣ ሆቴሎች፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ አምባሳደሮች እና የተለያዩ ተቋማት ይሳተፋሉ።