ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ብልጽግና ስናረጋግጥ ፍትህ እና የአኗኗር ዘዴ ትኩረት የምናደርግባቸው ጉዳዮች ናቸው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ መስከረም 30/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ብልጽግና ስናረጋግጥ ፍትህ እና የአኗኗር ዘዴ ትኩረት የምናደርግባቸው ጉዳዮች ናቸው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተጀመረውን የፍትህ አሰጣጥ ቴክኖሎጂ ዛሬ ጎብኝተዋል::

ከጉብኝቱ በኋል በሰጡት ማብራሪያ፤ የኢትዮጵያን ብልጽግና ስናረጋግጥ ፍትህ እና የአኗኗር ዘዴ ትኩረት የምናደርግባቸው ጉዳዮች ናቸው ብለዋል።

የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራተጂ የተቀረጸው የፋይናንስ፣ የንግድ፣ የጸጥታ ተቋማትን ጨምሮ በርካታ ተቋማት የማሽን ግብዓት በመጠቀም አገልግሎትን እንዲያጠናክሩ ለማስቻል መሆኑንም ገልጸዋል።


 

ፍትሕ በተለያየ መንገድ የሚገዛ በመሆኑ ፍትሕ እና ርትዕን ለማረጋገጥ አንዱ መፍትሄ የኦቶሜሽን አሰራር ስርዓት መዘርጋት እንደሆነም አንስተዋል።

ችሎትን የተለያዩ አካባቢዎች ላይ ሆኖ በመከታተል ፍትሕን ማግኘት ትልቅ ዕድል መሆኑን ጠቁመው፤ ባለጉዳዮች ካሉበት ቦታ ሆነው ፍትሕ ማግኘታቸው በጊዜና በገንዘብ የማይለካ ጥቅም ያለው መሆኑንም ገልጸዋል።

ከዚህ አንጻር የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰራው ስራ አስደማሚ መሆኑንና ይህንን ስርዓት በቅርንጫፎች ማዳረስ ተችሏል ብለዋል።

ከዚህም አልፎ ክልሎች ይህንን መንገድ እንዲከተሉ እያደረጉ ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው።

የኢትዮጵያን ብልጽግና ስናረጋግጥ ፍትህ እና የአኗኗር ዘዴ ትኩረት የምናደርግባቸው ጉዳዮች ናቸው ሲሉም ነው የገለጹት።


 

በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተጀመረው የፍትህ አሰጣጥ ቴክኖሎጂ በሁሉም አካባቢ ተዳርሶ ፍትህን ማጣጣም ያስፈልጋል ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።

በሀገሪቱ ያሉ የተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እየዘመኑ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ለአብነትም መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተጠቃሽ መሆኑን ገልጸዋል።

በሀገሪቱ እየተከናወነ ያለው የዲጂታላይዜሽን አሰራር ጠቀሜታው በስፋት እየታየ ይገኛል ሲሉም አክለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም