ቀጥታ፡

የመደመር ትውልድ መጽሐፍ በፓኪስታኑ ኡርዱ ቋንቋ ተተርጉሞ ለንባብ በቃ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 30/2018(ኢዜአ)፦ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጻፈው 'የመደመር ትውልድ' መጽሐፍ በፓኪስታኑ የስራ ቋንቋ ኡርዱ ተተርጉሞ ለንባብ ቀርቧል።

የመደመር ትውልድ መጽሐፍ የትርጉም ሥራ በፓኪስታን ብሔራዊ ቋንቋ ማስታወቂያ መምሪያ አማካኝነት የተከናወነ ሲሆን የፓኪስታን የባህልና ቅርስ ሚኒስትር አውራንግዜብ ካን ኺቺ ክትትል አድርገውበታል።

ይህ የትርጉም ሥራ በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) እና በፓኪስታን የባህልና ቅርስ ሚኒስትር አውራንግዜብ ካን ኺቺ መካከል የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎ የተከናወነ መሆኑ ተመላክቷል፡፡


 

በመጽሐፉ የምረቃ ሥነ ሥርዓት አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) የመጽሐፉ በኡርዱ ቋንቋ መዘጋጀት በፓኪስታን በሚገኙ የፖለቲካ ልሂቃን፣ ምሁራን እና ወጣቶች ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትን ያተረፈውን የመደመር ፍልስፍና በጥልቀት እንዲረዱ ትልቅ እድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የኡርዱኛ ተናጋሪዎች የመጽሐፉን ዋና መልዕክት በቀላሉ እንዲረዱ ብሎም ኢትዮጵያ የምትከተለውን የጋራ ብልጽግና አስተሳሰብ ለማስተዋወቅ ወሳኝ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡

አምባሳደር ጀማል በከር(ዶ/ር) የፓኪስታን ብሔራዊ ቋንቋ ማስታወቂያ መምሪያ ጽሕፈት ቤትን የጎበኙ ሲሆን የመጽሐፉን የኡርዱ ቋንቋ ቅጂ ከመምሪያው ዋና ዳይሬክተር መሐመድ ሳሊም ማዝሃር(ፕሮፌሰር) ተቀብለዋል።

የመጽሐፉ መተርጎም በኢትዮጵያና በፓኪስታን መካከል የተመሰረተው ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ውጤት ሲሆን ለቀጣይ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርም መሰረት የሚጥል እንደሆነ ተመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም