የመከላከያ ሠራዊት የማሻሻያ እርምጃ ዩኒቨርሲቲው ተልዕኮን በብቃት የሚወጣበትን ዕድል ፈጥሯል-ብርጋዴር ጄነራል ከበደ ረጋሳ - ኢዜአ አማርኛ
የመከላከያ ሠራዊት የማሻሻያ እርምጃ ዩኒቨርሲቲው ተልዕኮን በብቃት የሚወጣበትን ዕድል ፈጥሯል-ብርጋዴር ጄነራል ከበደ ረጋሳ

አዲስ አበባ፤መስከረም 30/2018(ኢዜአ)፦የመከላከያ ሠራዊት ተቋማዊ የማሻሻያ እርምጃ ዩኒቨርሲቲው ተልዕኮን በብቃት የሚወጣበትን ዕድል መፍጠሩን የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ብርጋዴር ጄነራል ከበደ ረጋሳ ገለጹ።
የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ለሁለት ቀናት በቢሾፍቱ ከተማ ያካሄደው የምርምር አስተዳደር፣ፈጠራና የማኅበረሰብ ተሳትፎ ጥናትና ምርምር ተሞክሮን ለመጋራት ያለመ የአውደ ጥናት አካሂዷል።
በአውደ ጥናቱ ማጠቃለያ ላይ የመከላከያ ሠራዊት ጄኔራል መኮንኖች፣ ምሁራን፣ የዩኒቨርሲቲው የስራ ኃላፊዎችና የጥናትና ምርምር ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ብርጋዴር ጄነራል ከበደ ረጋሳ፥አውደ ጥናቱ የሠራዊቱን የማድረግ አቅም ማጎልበት የሚያስችሉ ወሳኝ የጥናትና ምርምር ውጤቶች የተገኙበት ነው ብለዋል።
በዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ሥርዓት የጥናትና ምርምር መርሃ ግብሮችን በመቅረጽ የሠራዊቱን ሁለንተናዊ አቅም የሚያሻሽሉ የጥናትና ምርምር ስራዎችን እያከናወኑ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በዚህም የመከላከያ ሠራዊት ዘመኑን በዋጀ የጥናትና ምርምር ውጤቶች በአስተማማኝ ቁመና የተደራጀ ተቋም ማድረግ እንደተቻለም አስረድረተዋል።
የመከላከያ ሠራዊት የወሰዳቸው ወሳኝ ተቋማዊ የማሻሻያ እርምጃዎች ዩኒቨርሲቲው ተልዕኮን በብቃት እንዲወጣ እያስቻሉት እንደሚገኝ አብራርተዋል።
በቀጣይም በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በዕውቀትና ክህሎት የጥናትና ምርምር አቅምን ለማሳደግ ከተቋማት ጋር በመተባበር የመከላከያ ሠራዊትን የማድረግ አቅም የሚያጎለብቱ ስራዎች እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ኮሎኔል ሚኒሊክ ዋለ (ዶ/ር)፤ የመከላከያ ሠራዊትን የሚያዘምኑ የጥናትና የምርምር ውጤቶች እየተሰሩ ነው ብለዋል።
የጥናትና ምርምር አቅምን ለማሳደግም ከከፍተኛ የጥናትና ምርምር ትምህርት ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
አውደ ጥናቱም የተቀናጀ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በማከናወን ግብዓት የተገኘበት መሆኑን ተናግረዋል።
በአውደ ጥናቱ የተለያዩ ጸሁፎችን ካቀረቡ ምሁራን መካከል የባህርዳር ዩንቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስትቲዩት የሪሰርች እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ዳይሬክተር ሙሉቀን ዘገየ (ዶ/ር) ቴክኖሎጂዎች ችግር ፈቺ መሆን እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የምርምር ውጤቶች ወደ ተግባር እንዲሸጋገሩም በጋራ መስራት እንደሚገባ ገልጸው አንዱ መንገድም የምርምር መሰረተልማቶችን በጋራ መጠቀም መሆኑን እንስተዋል።
በቀጣይም ዩንቨርሲቲው በሚያከናውናቸው ስራዎች ውስጥ በጋራ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
በአውደ ጥናቱ በርካታ የልምድ ልውውጥ መደረጉን ያነሱት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የኢኖቬሽን እና ኢንጌጅመንት ዳይሬክተር ሰለሞን ኪሮስ (ዶ/ር) ናቸው።
በቀጣይም በላቀ ሁኔታ ከመከላከያ ዩንቨርሲቲ ጋር እንደሚሰሩ ተናግረዋል።