የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ ለሀገር ያለው ፋይዳ ዘርፈ ብዙ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ ለሀገር ያለው ፋይዳ ዘርፈ ብዙ ነው

አዲስ አበባ፤መስከረም 30/2018(ኢዜአ)፦የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ ለሀገር እድገት መፋጠን ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳለው የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ በመላ አገሪቷ ነገ ይጀመራል።
በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የአዲስ አበባ ስታቲስቲክስ ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ ተሰማ ኡርጌሳ ለኢዜአ እንዳሉት፥ በኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ የሚገኙ መረጃዎች በዘርፉ ለሚዘጋጁ እቅዶች፣ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎች በትክክለኛ ግብዓት ያገለግላሉ።
የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ ጥናት ጠቃሚ የመረጃ ግብዓት በማስገኘት በኢኮኖሚያዊ ልማት ላይ ያለው አበርክቶ የጎላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
እንደሥራ አስኪያጁ ገለጻ፤ በአዲስ አበባ ያሉ የንግድ ተቋማት እና ኢንዱስትሪዎች እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ያሉባቸውን ችግሮች በመለየት ጥናት በማድረግ ለፖሊሲ ግብዓትነት እንዲውል ለማድረግ ያግዛል ነው ያሉት፡፡
በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የቢዝነስ ስታቲስቲክስ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ናቃቸው ነጋሽ በበኩላቸው፥ የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ በሁሉም ክልሎች ያሉትን ድርጅቶች እና ሁሉንም የኢኮኖሚ አውታሮች ተደራሽ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።
በቆጠራ ስራው ለሚሰማሩ ባለሙያዎች ስልጠና የተሰጠ ሲሆን፤ ከጥቅምት 1 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በመላ ሀገሪቷ የቆጠራው የመስክ ስራ እንደሚጀመር ታውቋል፡፡
ሁሉም ዜጎችና የንግዱ ማኅበረሰብ የሚሰበሰበው መረጃ ለሀገር የሚጠቅም መሆኑን በመረዳት መረጃውን በመስጠትና በጎ ትብብር በማድረግ እንዲያግዙም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ላለፉት 25 ቀናት በመላ ሀገሪቷ በ56 የስልጠና ማዕከላት ሲሰጥ የቆየው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ ስልጠናን አጠናቋል፡፡