ቀጥታ፡

የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ለሚደረጉ ጥረቶች ስኬታማነት የሁሉም አካላትን ርብርብ ይጠይቃል - ሚኒስቴሩ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 30/2018(ኢዜአ)፦ የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚደረጉ ጥረቶች ስኬታማ እንዲሆኑ የሁሉም አካላት ርብርብ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ።

ብሔራዊ የአካል ጉዳተኞች ረቂቅ ፖሊሲ ላይ የመጨረሻ የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ ተካሂዷል።

የሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ መንግስት አካል ጉዳተኞችን በተሻለ መልኩ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያከናውናቸውን ተግባራት አጠናክሮ ይቀጥላል።


 

በአሁኑ ወቅትም የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት ማሳደግ የሚያስችሉ ፖሊሲዎችን፣ ሕጎችንና ስትራቴጂዎችን በማሻሻልና ግብዓት ተሰጥቶባቸው ስራ ላይ እንዲውሉ ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በሀገሪቱ የሚወጡ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች የአካል ጉዳተኞችን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት ማሳደግ የሚያስችሉ መሆናቸውንም ከጉዳዩ ባለቤቶች ጋር በመሆን እንደሚያረጋግጥ አንስተዋል።

የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ለመንግስት ብቻ የሚተው አይደለም የሚሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ የሚወጡ ሕጎችና ደንቦች ተግባራዊና ስኬታማ ለማድረግ የሁሉም አካላት ርብርብ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ለረዥም ጊዜ የአካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ረቂቅ ፖሊሲ ሲዘጋጅ በጥልቀት ውይይት ሲደረግበት የቆየ ሲሆን፤ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ግብዓት የሰጡበት መሆኑንም ተናግረዋል።


 

የፍቅር ኢትዮጵያ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ማሕበር ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ምሕረት ንጉሴ እንደተናገሩት፤ የፖሊሲው ዝግጅት አሳታፊና የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነው።

ረቂቅ ፖሊሲው በተለይም አካል ጉዳተኞች በየወቅቱ ሲያቀርቡት የነበረውን የትምህርት፣ የጤና እና ሌሎች ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥ ነው ብለዋል።

በረቂቅ ፖሊሲው ዝግጅት ወቅትም ለረዥም ጊዜ ሲካሔድ የቆየው ውይይት የጉዳዩ ባለቤቶችን ፍላጎትና ተጠቃሚነት ለማካተት ያስቻለ እንደሆነም ጠቅሰዋል።


 

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን የቦርድ ሰብሳቢ መላኩ ጉለጫ በበኩላቸው፤ ፖሊሲው አካል ጉዳተኛውን በጉዳቱ ልክ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል ነው ብለዋል።

በረቂቅ ፖሊሲ ዝግጅቱ ወቅት የአካል ጉዳተኞች ማሕበራት ተወካዩች የተሳተፉ ሲሆን፤ ፖሊሲው ፀድቆ ስራ ላይ ሲውል ወጥ በሆነ መንገድ ችግሮችን ማቃለል የሚያስችል መሆኑንም ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም