ቀጥታ፡

ሠንደቅ ዓላማችን ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን በመላበስ ጠንካራ ሀገረ መንግስት የመገንባት አርማችን ነው

ባህር ዳር፤ መስከረም 30/2018(ኢዜአ)፦ ሠንደቅ ዓላማችን ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን በመላበስ ጠንካራ ሀገረ መንግስት የመገንባት አርማችን ነው ሲሉ የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሰጤ ገለፁ።

የፊታችን ሰኞ የሚከበረውን የሠንደቅ ዓላማ ቀን ምክንያት በማድረግ ምክትል አፈ-ጉባኤው ዛሬ በባህር ዳር መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም፤ ሠንደቅ ዓላማ የቀደሙ አባቶቻችን ለሀገራቸው ክብር ሲሉ በጀግንነት መስዋዕትነት የከፈሉበትና ነፃነትን ያጎናፀፈ አርማ መሆኑን ተናግረዋል።

ሠንደቅ ዓላማችን ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን በመላበስ ጠንካራ ሀገረ መንግስትን የመገንባት አርማችን ነው ሲሉም አክለዋል።

በዓሉ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕደሴ ግድብ የተጠናቀቀበትና ሌሎች ታላላቅ አዳዲስ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች በተበሰሩበት እንዲሁም የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመን ላይ የሚከበር በመሆኑም ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።

በመሆኑም የሠንደቅ ዓላማ ቀንን በክልሉ በሚገኙ ዞኞች፣ ከተሞችና ወረዳዎች በድምቀት ማክበር የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን ገልፀዋል።

በክልሉ ዘላቂ ልማትን ለማስመዝገብ የ25 ዓመት አሻጋሪ የልማት ዕቅድና የ5 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ወደ ትግበራ በማስገባት የላቀ ውጤት ለማስመዝገብም በየደረጃው ከሚገኙ ሰራተኞች ጋር ቃል የሚገባበት እንደሆነም አብራርተዋል።

እንዲሁም በክልሉ ዘላቂ ሰላም ለመገንባት በሚደረገው ርብርብ ዙሪያ ሰራተኞች ሚናቸውን እንዲወጡ በሠንደቅ ዓላማው ፊት በመቆም ቃል የሚገቡበት እንደሆነም አስረድተዋል።

ቀኑ በውይይት፣ ልዩ ልዩ የኪነ-ጥበብ ስራዎችን በማቅረብ፣ ከረፋዱ 4 ሰዓት ሠንዳቅ ዓላማ በክብር በመስቀልና በሌሎች ዝግጅቶች እንደሚከበርም አስታውቀዋል።

ለ18ኛ ጊዜ የሚከበረውን ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን በተሟላ መንገድ በድምቀት ለማክበር ተገቢው ዝግጅት መደረጉንና ለዚህ ማስፈፀሚያ የሚሆን ዝርዝር ዕቅድ መዘጋጀቱንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም