ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ትራንስፖርት ያሏትን ተሞክሮዎች የምታቀርብበት አህጉራዊ ሁነት

አዲስ አበባ፤ መስከረም 30/2018 (ኢዜአ)፦ “ አፍሪካ ኢ-ሞቢሊቲ ዊክ 2025” የተሰኘ የአፍሪካ የአረንጓዴ ትራንስፖርት ሳምንት ከጥቅምት 4 እስከ 6 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይደረጋል።

ሳምንቱ “ በአፍሪካ ሁሉን አቀፍ እና ዘላቂ የትራንስፖርት ስርዓትን ማረጋገጥ” በሚል መሪ ሀሳብ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ) ይካሄዳል። 

ተቀማጭነቱን ኬንያ ናይሮቢ ያደረገው ”አፍሪካ ኢ-ሞቢሊቲ አሊያንስ” የተሰኘ ድርጅት፣ የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር፣ የተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም እና ሌሎች አጋሮች ሁነቱን በጋራ አዘጋጅተዋል።


 

በሁነቱ ላይ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ኢኖቬተሮች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ባለሀብቶች፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና የትራንስፖርት ዘርፍ መሪ ተዋናያን ይሳተፋበታል።

ሳምንቱ አፍሪካ ወደ ኤሌክትሪክ ተሽርካሪዎች የምታደርገውን ሽግግር ማፋጠን ዋንኛ ትኩረቱ አድርጓል። 

የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ በርኦ ሀሰን በአረንጓዴ ትራንስፖርት ሳምንቱ ላይ ከ500 በላይ ሰዎች በአካል እና ከ2000 በላይ ሰዎች በበይነ መረብ አማራጭ እንደሚሳተፉ ለኢዜአ ገልጸዋል።

በሳምንቱ ላይ ከ30 በላይ የውይይት መድረኮች እና አውደ ርዕዮች እንደሚካሄዱ ጠቅሰው ከነዚህም አንዱ የአፍሪካ ሀገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት የሚገኙበት መድረክ እንደሆነ ተናግረዋል። 

አረንጓዴ ትራንስፖርትን የተመለከቱ የጥናት ውጤቶች እና ግኝቶች ይፋ እንደሚደረጉም ነው የገለጹት።

ከሁነቶቹ ጎን ለጎን የኢንዱስትሪ ጉብኝት መርሃ ግብር እንደሚኖር ጠቅሰው ከ200 በላይ ተሳታፊዎች የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ገጣጣሚዎችን፣ የኤሌክትሪክ ባሶች እንቅስቃሴ፣ የተሰሩ የኃይል መሙያ ማዕከላት፣ ዴፖዎች እንዲሁም በሽያጭ፣ አቅርቦት እና ጥገና የተሰማሩ አካላትን እንቅስቃሴ እንደሚጎበኙ አመልክተዋል። 

በ2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተካሄደው “ኢትዮ ግሪን ሞቢሊቲ 2024” ዓለም አቀፍ አውደ ርዕይና ሲምፖዚየም ላይ የተነሱ አጀንዳዎች አፈጻጸም እንደሚገመገምም እንዲሁ። 

የትራንስፖርት ሳምንቱ አካል የሆነ የ1 ሺህ 600 ኪሎ ሜትር የኤሌክትሪክ መኪና ጉዞ በመካሄድ ላይ መሆኑን ጠቅሰው ተጓዦቹ ዛሬ ሶስተኛ ቀናቸውን እንደያዙና የፊታችን እሁድ አዳማ እንደሚደርሱ ጠቁመዋል።

ጉዞው በኤሌክትሪክ መኪናዎች አማካኝነት ቀጣናዊ የትራንስፖርት ስርዓትን መፍጠርን ያለመ ነው ብለዋል። 

ኢትዮጵያ በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ በማድረግ  በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን የማስፋት ስራ እያከናወነች እንደምትገኝም ነው ሚኒስትር ዴኤታው የገለጹት።

በኢትዮጵያ መንገዶች ላይ ካሉ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ተሽከርካሪዎች መካከል ከ115 ሺህ በላይ የኤሌክትሪክ መኪኖች እንደሚገኙበት ጠቁመው ይህም ከአጠቃላይ ተሽከርካሪዎች የሰባት መቶ ድርሻ እንደያዙ ጠቁመዋል። 

የግሉን ዘርፍ እና የተለያዩ አካላትን በማሳተፍ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የተሽከርካሪዎች ኃይል መሙያ ጣቢያዎች መገንባታቸውን ነው ያብራሩት። 

በኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት 16 ተቋማት የኤሌክትሪክ መኪናዎችን እየገጣጠሙ መሆናቸውን ጠቅሰው የአረንጓዴ ትራንስፖርት በህዝብ ትራንስፖርት ላይ እየሰፋ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የኤሌክትሪክ አውቶቢሶች የማስፋት ስራ ውጤት እያስገኘ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው መንግስት በኤሌክትሪክ መኪና ለተሰማሩ አካላት የታክስ ማበረታቻ ማድረጉንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ትራንስፖርት በፖሊሲ እና ስትራቴጂ በመደገፍ ውጤታማ ስራን እያከናወነች እንደምትገኝና ይህንንም መልካም ተሞክሮዋን በአህጉራዊው ሁነት ላይ እንደምታቀርብ አመልክተዋል። 

የትራንስፖርት ሳምንቱ አካል የሆነ የወጣቶች ጉባኤ በበይነ መረብ መካሄዱንና በዚህም መደረክ ላይ ኢትዮጵያ ያላትን ተሞክሮ ለአፍሪካ ሀገራት ማቅረቧን ገልጸዋል።  

የአፍሪካ አረንጓዴ ትራንስፖርት ሳምንት አህጉሪቷ ከብክለት የጸዳ የአረንጓዴ ትራንስፖርት ስርዓት ለመፍጠር ለምታደርገው ጥረት አቅም የሚፈጥር መሆኑ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም