በወላይታ ዞን የቡና ጥራትን የበለጠ በማስጠበቅ የዘርፉን ተዋንያን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በወላይታ ዞን የቡና ጥራትን የበለጠ በማስጠበቅ የዘርፉን ተዋንያን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል

ወላይታ ሶዶ፤ መስከረም 30/2018(ኢዜአ)፦ በወላይታ ዞን የቡና ጥራትን የበለጠ በማስጠበቅ የዘርፉን ተዋንያን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት መሰጠቱን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።
በወላይታ ዞን የ2018 የቡና ጥራት ቁጥጥር ግብይት አስተባባሪ ግብረ-ኃይል ንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል።
በመድረኩ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ሳሙኤል ተሰማ የቡና ጥራትና ሕጋዊ ግብይትን በማስጠበቅ የዘርፉን ተዋንያን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
የቡና ምርት ጥራትን ማስጠበቅ የዘርፉን ተዋንያን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ከማሳደግ ባሻገር የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለመጨመር ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ጠቅሰዋል።
የቡና ጥራትን የበለጠ ከማስጠበቅ በተጓዳኝ ምርታማነትን ለማሳደግ የተሻሻሉ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ የማቅረብ፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያ አጠቃቀምን የማጎልበት፣ ያረጁ የቡና ዛፎችን የመጎንደልና በአዲስ የመተካት ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል።
በቡና ንግድ ላይ የሚስተዋል ህገ-ወጥ ግብይትን መከላከል የሚያስችል የቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋቱንም ተናግረዋል።
ለቡና ምርት ልዩ ትኩረት በመስጠት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ የብልጽግናን ጉዞ ዕውን ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል ያሉት ደግሞ የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ ዘማች ሶርሳ(ዶ/ር) ናቸው።
የዞኑ ቡና በራሱ ስያሜ ለማዕከላዊ ገበያ እንዲቀርብ ፈቃድ ተሰጥቶ እየተሰራበት ስለመሆኑ አንስተዋል፡፡
ከለቀማ እስከ አስተሻሸግ እንዲሁም ወደ ማዕከላዊ ገበያ እስከሚገባ ድረስ ያለውን የጥራት ደረጃ ለማስጠበቅ ለአርሶ አደሮችና በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሀብቶች ግንዛቤ መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡
ደረጃውን የጠበቀ ምርት ለመሰብሰብ እሸት ቡናን የመልቀም፣ የአደራረቅና አስተሻሸግን ጨምሮ የማጓጓዝ እንዲሁም የክምችት ስራውን በጥንቃቄ የመምራት ተግባር መከናወኑን አስረድተዋል፡፡
በዞኑ ባለፈው በጀት ዓመት ከ1ሺህ 677 በላይ ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ የቀረበ ሲሆን በ2018 ዓ.ም ከ2ሺህ 116 በላይ ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ መታቀዱንም ሃላፊው አመልክተዋል።
ምርቱን ጥራት ባለው መልኩ ለማዘጋጀትም በዞኑ የሚገኙ 12 የቡና መፈልፈያ ኢንዱስትሪዎች ዝግጅት ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።
በዚህም ባለፈው የምርት ዘመን በአተገባበር ላይ የተስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ በ2018 በጀት ዓመት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።
በመድረኩ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።