በጋምቤላ ክልል ብሔራዊ ክብርና አርማ የሆነው የሰንደቅ ዓላማ ቀን በድምቀት ይከበራል - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል ብሔራዊ ክብርና አርማ የሆነው የሰንደቅ ዓላማ ቀን በድምቀት ይከበራል

ጋምቤላ ፤መስከረም 30/2018 (ኢዜአ)፡- በጋምቤላ ክልል ብሔራዊ ክብርና አርማ የሆነውን የሰንደቅ ዓላማ ቀን በድምቀት እንደሚከበር የክልሉ ምክር ቤት አፈ- ጉባኤ ወይዘሮ መሰረት ማቲዎስ ገለጹ።
በጋምቤላ ክልል የዘንድሮውን የሰንደቅ ዓላማ ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች ለማክበር ዝግጅት ተደርጓል።
የአፈ- ጉባኤዋ ዕለቱን አስመልክተው እንደገለጹት የብሔራዊ ክብርና አርማ የሆነውን የሰንደቅ ዓላማ ቀን ከክልል ደረጃ ጀምሮ እስከ ወረዳ በድምቀት ለማክብር አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል።
የሰንደቅ ዓላማ ቀን ከነገ ጥቅምት 1 ቀን 2018 ጀምሮ የህዝቡን በተለይም ወጣቱ የሰንደቅ ዓላማን ምንነት፣ ትርጉምና ክብር በአግባቡ እንዲረዳ በፓናል ውይይትና ሌሎች ዝግጅቶች እንደሚከበር ገልጸዋል።
በጥቅምት 3 ቀን 2018 ዓ.ም ከጧት 4:30 በጋምቤላ ከተማ አደባባይና በሁሉም የዞንና የወረዳ ከተሞች በተመሳሳይ ስዓት አመራሩ በተገኘበት የሰንደቅ ዓላማ የመስቀል ስነ- ስርዓት ይካሄዳል ብለዋል።
የዘንድሮው የሰንደቅ ዓላማ ቀን እንደ ሀገር በርካታ የልማት ስኬቶችና የማንሰራራት ጅማሮ በተበሰረበት ማግስት የሚከበር መሆኑ ልዩ ትርጉም ያለው መሆኑን አፈ- ጉባኤዋ ገልጸዋል።