የክልሉን ህዝብ ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎች ይጠናከራሉ- ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
የክልሉን ህዝብ ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎች ይጠናከራሉ- ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

አርባምንጭ፤መስከረም 30/2018 (ኢዜአ) :-በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተያዘው የበጀት ዓመት የክልሉን ህዝብ ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎች እንደሚጠናከሩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ አስታወቁ።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት እና የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የጋራ መክፈቻ ስነ-ስርአት በአርባምንጭ ከተማ ተካሂዷል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በመክፈቻ ስነ-ስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር እንዳሉት፥ ባለፈው በጀት ዓመት ክልሉን የሰላም፣ የመቻቻልና የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት ውጤት የተመዘገበባቸው ናቸው።
በዚህም በክልሉ የተረጋጋ ሰላም የሰፈነ ሲሆን በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፖለቲካ ዘርፎች የህዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።
በተያዘው በጀት ዓመትም የክልሉን ኢኮኖሚ በተሻለ መልኩ ለማሳደግ እንደሚሰራ ገልጸው፥ አስፈጻሚ አካላትም በመፍጠርና በመፍጠን እንዲሁም በመደመር እሳቤ በተሰማሩበት መስክ ውጤት ሊያስመዘግቡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ክልሉ ሰፊ የሰውና ተፈጥሮ ፀጋ ያለበት መሆኑን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ይህን ፀጋ በተቀናጀ መንገድ ወደ ውጤት ለመቀየር የተጀመሩ ተስፋ ሰጪ ተግባራት በዘንድሮም ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
በተለይ የግብርና ዘርፉን በኩታ ገጠም የአመራረት ዘዴ በመደገፍ በመጠን፣ በጥራትና ምርታማነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
የሌማት ትሩፋት ሥራ እንደሚጠናከር ጠቅሰው፥ ክልላዊ ገቢ የመሰብሰብ አቅምን ማሳደግ እንዲሁም የቱሪዝምና የማዕድን ፀጋዎችን በማልማት ከዘርፉ ተገቢውን ጥቅም ለማግኘት በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በተጨማሪም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ የሚደረገውን ቁጥጥር በማጠናከር ገበያን ለማረጋጋት የሚከናወኑ ተግባራት የሚቀጥሉ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
በክልሉ በ13 ከተሞች የኮሪደር ልማት ስራ እየተካሄደ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ጥላሁን፥ ይህን ስራ ከማስፋፋት ጎን ለጎን የገጠር ኮሪደር ልማትም በትኩረት የሚከናወን መሆኑን አውስተዋል።
አቶ ጥላሁን በንግግራቸው፥ የክልሉን ህዝብ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት አሁን ካለበት 52 በመቶ ወደ 55 በመቶ ማሳደግ እንዲሁም በአርብቶ አደር አካባቢ የሚከናወኑ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት ስራዎችም ይጠናክራሉ ብለዋል።
በመክፈቻ ጉባኤው ላይ የክልሉ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አለማየሁ ባውዲ እና የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አዳማ ትንጳዬን ጨምሮ የሁለቱ ምክር ቤት አባላት፣ሥራ አስፈጻሚዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት አባቶች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።