ቀጥታ፡

በድሬደዋ የኢንደስትሪዎችን አቅም በማሳደግ በተፈጠረው የስራ ዕድል ተጠቃሚ ሆነናል -ወጣቶች

ድሬደዋ፣ መስከረም 30/2018(ኢዜአ)፡- በድሬደዋ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንደስትሪዎችን አቅም በማሳደግ በተፈጠረው የስራ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ወጣቶች ተናገሩ።

የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች ቡድን  ትላንት በድሬዳዋ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ  ወደ ስራ የገቡ 11 የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ስራ ያስጀመሩ ሲሆን ኢንደስትሪዎቹ ከ1500 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የስራ ዕድል መፍጠራቸው በወቅቱ ተመላክቷል።

ተመርቀው ወደስራ በገቡ ኢንደስትሪዎች የስራ ዕድል የተፈጠረላቸው የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ምሩቃን ለኢዜአ እንደተናገሩት በኢንዱስትሪዎቹ በተፈጠረላቸው ይሰራ እድል ተጠቃሚ ሆነዋል።

ከስራ ዕድል ተጠቃሚዎች መካከል  በኢንጂነሪንግ የተመረቀው ወጣት አገኘሁ አለማየሁ  እንደገለፀው፤ መንግስት የኢንደስትሪዎችን የማምረት አቅም ለማሳደግ የቀየሰው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አማካኝነት የስራ እድሉ ተጠቃሚ ሆኗል። 

በኢትዮጵያ ታምርት ወደ ስራ የገባው  የቆርቆሮ ፋብሪካ  ለጀማሪዎች የስራ እድል በመፍጠሩ ለእሱና ለሌሎች ወጣቶች የስራ ዕድል  መክፈቱን አክሏል።

በከተማዋ አዲስ  በተከፈተው የዱቄት ፋብሪካ የስራ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ አቶ ምንዳ ኡርጌሳ፣ በድሬዳዋ የኢንደስትሪዎች መነቃቃት ለስራ ፈላጊውም ጭምር አስተዋፅኦ  በማድረጉ ከስራ እድሉ ተጠቃሚ መሆኑን ጠቁሟል።

ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ የተመረቀው ወጣት ሙርቴይሳ መሐመድ በበኩሉ በመንግስትና በባለሀብቶች ቅንጅት የተተገበረው የኢንቨስትመንት  ማስፋፋት  ለድሬዳዋ ዕድገት እና ለወጣቶች ተጠቃሚነት  ወሳኝ እየሆነ መጥቷል ብሏል።

እሱም ይሄን እድል በመጠቀም በተማረበት ሙያ ወደ ስራ መግባቱን አስረድቷል።

''የማዳበሪያ ከረጢት ፋብሪካ ወደ ስራ መግባቱ ለእኔና ለብዙ ሴቶች የስራ ዕድል ፈጥሮልናል'' ያለችው ደግሞ ወጣት ማርታ ዋቅጅራ ናት።

ከተማ አስተዳደሩ ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት ለአገር ዘላቂ ልማትና ለስራ እድል ፈጠራ ተጨማሪ አቅም መፍጠሩን ተናግራለች።

የፋብሪካዎቹ ስራ መጀመርም የወጣቶች የስራ ዕድል  ጥያቄን ለመመለስ እያገዘ መሆኑን ተናግራለች።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም