ቀጥታ፡

የጀግንነት፣ የነፃነትና የህብር ብሔራዊ አንድነት መገለጫ የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ በማክበር የሀገርን ከፍታ ክብርና ሉዓላዊነት ማስቀጠል ይገባል

ጋምቤላ፤ መስከረም 30/2018(ኢዜአ) የጀግንነት፣ የነፃነትና የህብር ብሔራዊ አንድነት መገለጫ የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ በማክበር የሀገርን ከፍታ ክብርና ሉዓላዊነት ማስቀጠል ይገባል ሲሉ በጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎችና የተለያዩ የጸጥታ አካላት ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከኢትዮጵያ ባለፈ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ምልክት ተደርጎ በብዙዎች ዘንድ ይነሳል።

ለዚህም በአፍሪካ በርካታ ሀገራት ቀለሙን በመጋራት በተለያዩ አቀማመጦችና ምልክቶች እየተጠቀሙበት ዘመናትን ተሻግረዋል።

በመሆኑም የፊታችን ሰኞ የሚከበረውን የሰንደቅ አላማ ቀን ምክንያት በማድረግ የኢዜአ ሪፖርተር በጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎችንና የጸጥታ አካላትን አነጋግሯል።

አስተያየት ሰጪዎቹም የጀግንነት፣ የነፃነትና የህብር ብሔራዊ አንድነት መገለጫ የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ በማክበር የሀገርን ከፍታ ክብርና ሉዓላዊነት ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ፒተር አማን፤ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ክብሩ እና መገለጫነቱ ከሀገርም የተሻገረ የነፃነት ምልክት ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑን ገልጸዋል።

ለኢትዮጵያውያን ሰንደቅ ዓላማ የጀግንነት፣ የአሸናፊነት፣ የአይበገሬነትና የነፃነት ምልክት ሆኖ የሚታይ መሆኑን አንስተው በዚሁ ልክ ክብር መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

የቀድሞው አባቶች ’’ተመልከት ዓላማህን ተከተል አለቃህን’’ በሚል ብሂል የውጭ ወራሪን ሲመክቱ ሰንደቅ ዓላማቸውን በማስቀደም ነበር ያሉት አስተያየት ሰጪው አባቶች በመስዋዕትነት ያቆትን ታሪክ ለቀጣዩ ተውልድ በክብር ማስረከብ ይገባል ብለዋል። 


 

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ በስፋት መንግስቴ ከጥንት ጀምሮ ለሰንደቅ ዓለማ ደምና አጥንታቸውን ገብረው የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ክብር ያስጠበቁበት አርማ በመሆኑ ይህንን ታሪክ ከነክብሩ ማዝለቅ ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።


 

ከክልሉ ፖሊስ አባላት መካከል ረዳት ኢንስፔክተር ተስፋዓለም ዘለቀ እና ዋና ሳጅን ቶክ ቦት፤ ሰንደቅ ዓለማ የሀገር ክብር መገለጫና የቃል ኪዳናችን አርማ በመሆኑ ልዩ ክብርና ትርጉም እንሰጠዋለን ብለዋል።


 

በፖሊስነት ሙያቸው ሀገራቸውንና ህዝባቸውን ለማገልገል በሰንደቅ አላማው ፊት ቃለ-መሃላ ፈፅመው መግባታቸውን አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም