የደምና አጥንት ዋጋ የተከፈለበት ሰንደቅ ዓላማ የሀገር ክብርና ፍቅር መገለጫ በመሆኑ ትውልዱ ሊጠብቀው ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የደምና አጥንት ዋጋ የተከፈለበት ሰንደቅ ዓላማ የሀገር ክብርና ፍቅር መገለጫ በመሆኑ ትውልዱ ሊጠብቀው ይገባል

ሀዋሳ፤ መስከረም 30/2018(ኢዜአ)፦ በጀግኖች አባቶችና እናቶች የደምና አጥንት ዋጋ የተከፈለበት ሰንደቅ ዓላማ የሀገር ክብርና ፍቅር መገለጫ በመሆኑ ትውልዱ ሊጠብቀው ይገባል ሲሉ በሲዳማ ክልል የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር አባላት ገለጹ።
የዘንድሮው የሰንደቅ ዓላማ ቀን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቆ ታሪክ በተጻፈበት ወቅት መከበሩ የተለየ እንደሚያደርገውም ተመላክቷል።
በሲዳማ ክልል የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ሊቀመንበር የኋላእሸት ቸርነት ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በተለያዩ ጊዜያት የተቃጣባትን ወረራ በመመከት ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ ለኖረችው ኢትዮጵያ የሰንደቅ ዓላማ ቀንን ማክበር ትልቅ ትርጉም አለው፡፡
የሀገር ፍቅርና ክብር የሚገለጽበት ሰንደቅ ዓላማ በትውልድ ቅብብሎሽ ጸንቶ የሚቆይ መሆኑን ገልጸው፣ ቀኑን ማክበር በተለይ አዲሱ ትውልድ ለሀገርና ለባንዲራ የተከፈለን ዋጋ በአግባቡ እንዲረዳ ያግዛል ብለዋል፡፡
ጀግኖች አባቶችና እናቶች ለሀገር ነጻነትና ሉዓላዊነት የደምና አጥንት ዋጋ በመክፈል ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ከፍ እንዳደረጉ ሁሉ የአሁኑ ትውልድም የሕዳሴው ግድብን በድል በማጠናቀቅ የአባቶቹን ታሪክ እያስቀጠለ መሆኑን ተናግረዋል።፡
የዘንድሮ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ ፋይዳ የሚኖራቸው ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶች በተጀመሩበት ወቅት መከበሩ ትውልድን ለልማት እንደሚያነሳሳ ገልጸው፣ ትውልዱ አሁን የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በማጠናቅቅ የሀገሩን ሰንደቅ ዓላማ ዳግም ከፍ ማድረግ አለበት ብለዋል፡፡
የማህበሩ ጸሐፊ ወይዘሮ የሺ ለማ በበኩላቸው ሰንደቅ ዓላማ የሀገር ክብር መገለጫ፣ መለያና የነጻታቸን ምልክት በመሆኑ ተገቢውን ክብር ሰጥቶ ቀኑን ማክበሩ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል።
ለሀገርና ለባንዲራ ክብር ሲሉ ጀግኖች አባቶችና እናቶች እስከ ህይወት መስዋዕትነት ድረስ መክፈላቸውን አስታውሰው፣ ወጣቱ ትውልድም በመስዋዕትነት ጭምር ተከብራ የቆየችውን ኢትዮጵያን ሉዓላዊነቷን ጠብቆ ማቆየት እንዳበት ተናግረዋል።
የዘንድሮው የሰንደቅ ዓላማ ቀን በመጪው ጥቅምት 3 ቀን 2018 ዓ.ም በተለያዩ ዝግጅቶች በሀገር አቀፍ ደረጃ ይከበራል።