የሀገር ሉዓላዊነት ምልክትና የህዝቦች ነፃነት ማሳያ የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ ልንጠብቀው ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የሀገር ሉዓላዊነት ምልክትና የህዝቦች ነፃነት ማሳያ የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ ልንጠብቀው ይገባል

ሐረር፤ መስከረም 30/2018 (ኢዜአ)፡- የሀገር ሉዓላዊነት ምልክትና የህዝቦች የነፃነት ማሳያ የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ ልንጠብቀው ይገባል ሲሉ የሐረር ከተማ ነዋሪዎችና የፀጥታ አካላት ተናገሩ።
የፊታችን ጥቅምት 3 ቀን 2018 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከበረውን የሰንደቅ ዓላማ ቀን በማስመልከት ኢዜአ ያነጋገራቸው የሐረር ከተማ ነዋሪዎች የሀገር ሉዓላዊነት ምልክትና የህዝቦች ነፃነት ማሳያ የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ ልንጠብቀውና ልንከባከበው ይገባል ብለዋል።
በሀገር መከላከያ ሠራዊት የምስራቅ ዕዝ አባል የሆኑት ሻላቃባሻ ውባለም ጥጋቤ እና ምክትል አስር አለቃ ሜላት ደቦጭ፣ ሠራዊቱ ለአገር ሰላም እና ለህዝቦች አንድነት ቃለ መሃላ የፈጸመው በሰንደቅ ዓላማ ፊት ነው ብለዋል።
በዚሁ መነሻነት የሠራዊት አባል ለሰንደቅ ዓላማ የተለየ ትርጉም አለው፣ ግዳጅ ስትቀበል እስከ ህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ቀደምት አያቶቻችንና አባቶቻችን ያወረሱን አገርና ሰንደቅ ዓላማ በክብር ለቀጣይ ትውልድ እናስረክባለን ያሉት የሠራዊት አባላቱ የአገር ሉዓላዊነትና ክብር መገለጫ የሆነውን ሰንደቅ ዓላማን ማክበር ሁሉንም የሚያኮራና ለቀጣዩ ትውልድ ጀግንነትንና ሀገርን ማስረከብ መሆኑን ገልጸዋል።
ሌላው የሐረሪ ክልል ፖሊስ አባል ዋና ሳጅን ዮሐንስ አሻግሬ በበኩላቸው "አባቶቻቸን የህይወት መስዋዕትነት በመክፈል የሀገር ሉአላዊነት ያስከበሩት ለሰንደቅ ዓላማ ክብር ሲሉ ነው" ብለዋል።
የክልሉ ፖሊስም ጠዋትና ማታ በብሔራዊ መዝሙር ሰንደቅ ዓላማን በመስቀልና በማውረድ ከራሱ ባለፈ በህብረተሰቡ ውስጥ የሰንደቅ ዓላማ ፍቅር እንዲሰርጽ እያደረገ መሆኑን አንስተዋል።
እንደ ዋና ሳጅን ዮሐንስ ገለጻ የቀኑ መከበር ደግሞ በተለይ ለአዲሱ ትውልድ የሰንደቅ ዓላማ ፍቅርና ክብር በማስረጽ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጾ ያበረክታል።
ሰንደቅ ዓላማ የነጻነታችን፣ የኩራታችንና የአብሮነታችን ምልክት ነው ያሉት ደግሞ መምህርት አያንቱ ጫልጪሳ ናቸው።
የኢትዮጵያውያን አብሮነትና የነጻነት ምልክታችን የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ አክብሮና አስከብሮ ለተተኪው ትውልድ ማስተላለፍ የሁሉም ዜጋ ድርሻ መሆን አለበት ብለዋል።
አቶ ተስፋዬ ረጋሳም አባቶቻቸንን ለሰንደቅ ዓላማ ሲሉ በከፈሉት የአጥንት፣ የደምና የህይወት መስዋዕትነት የተከበረች ሀገር አስረክበውናል፤ እኛም ክብሯን ጠብቀን ለትውልድ ማቆየት አለብን ብለዋል።