በኢትዮጵያ የመድሃኒትና የጤና አገልግሎት ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ የመተካት ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል - ባለስልጣኑ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የመድሃኒትና የጤና አገልግሎት ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ የመተካት ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል - ባለስልጣኑ
ጅግጅጋ፤ መስከረም 30/2018(ኢዜአ)፦ የመድሃኒትና የጤና አገልግሎት ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ የመተካት ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን አስታወቀ።
ሀገር አቀፍ የምግብና የጤና ግብዓቶች ቁጥጥር ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በጅግጅጋ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በጉባኤው መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባ፤ በፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ ዘርፍ የታየው ለውጥ እመርታ የታየበት መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም በመድሃኒትና የተለያዩ የጤና ግብዓቶችን በማምረት ረገድ ከነበረበት ዝቅተኛ አፈፃፀም አሁን ከፍተኛ መሻሻል ማሳየቱን አንስተዋል።
በኢትዮጵያ የክትባት አምራች ተቋማትን ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን አንስተው በቀጣይ 60 በመቶ የክትባት ፍላጎትን በሀገር ውስጥ የመተካት ትልም በመሰነቅ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
በቀጣይም የመድሃኒትና የጤና አገልግሎት ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ምርት የመተካት ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ገልጸዋል።
ጉባኤው ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን የክልልና የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የስራ ሃላፊዎች ሪፖርት የሚያቀርቡ ይሆናል።