የዘንድሮ የሠንደቅ ዓላማ ቀን በአዲሱ ትውልድ ታሪክ ሰሪነት ኢትዮጵያ ታላቅ ክብርና ልዕልና በተጎናጸፈችበት ወቅት መከበሩ ልዩ ያደርገዋል - ኢዜአ አማርኛ
የዘንድሮ የሠንደቅ ዓላማ ቀን በአዲሱ ትውልድ ታሪክ ሰሪነት ኢትዮጵያ ታላቅ ክብርና ልዕልና በተጎናጸፈችበት ወቅት መከበሩ ልዩ ያደርገዋል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 30/2018(ኢዜአ)፦የዘንድሮ የሠንደቅ ዓላማ ቀን በአዲሱ ትውልድ ታሪክ ሰሪነት ኢትዮጵያ ታላቅ ክብርና ልዕልና በተጎናጸፈችበት ወቅት መከበሩ ልዩ ክስተት መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን በየዓመቱ የጥቅምት ወር በገባ የመጀመሪያው ሳምንት ሰኞ በመላ ሀገሪቱ በተለያየ ዝግጅቶች በታላቅ ድምቀት እንደሚከበር ይታወቃል።
የዘንድሮው የ2018 ዓ.ም 18ኛው የሠንደቅ ዓላማ ቀንም በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በተለያዩ ዝግጅቶች በመጪው ሰኞ ጥቅምት 03 ቀን 2018 ዓ.ም በድምቀት እንደሚከበር ይጠበቃል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እውነቴ አለነ፤ የዘንድሮው የሠንደቅ ዓላማ ቀን የትውልዱ የህብረ ብሔራዊነት አሻራ ያረፈበት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተጠናቀቀበት ማግስት መከበሩ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ ዜጎች የብዝኅ አንድነትን በማስጠበቅ በሁሉም መስክ ለሀገራቸው የከፈሉትን መስዋዕትነት የሚያሳይ የጋራ ምልክታቸው መሆኑን ተናግረዋል።
በታላቁ ህዳሴ ግድብ ምርቃት የተበሰሩ የሠንደቅ ዓላማ ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችም የኢትዮጵያን የብልጽግና ከፍታ በተሻለ መሠረት የሚያስቀምጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አብርሃም ዓለማየሁ (ዶ/ር)፤ የሠንደቅ ዓላማ ቀለም የአንድ የሀገር የኢኮኖሚ፣ የሰው ሃብትና የስልጣኔ ደረጃ መለያ ምልክትና መገለጫ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማም የዓለም ቀደምት ስልጣኔ ገናና ታሪክ፣ የአፍሪካና የጥቁር ህዝቦች በቅኝ አለመገዛት የነፃነት ተምሳሌታዊ ምልክት ተደርጎ እንደሚወሰድ ገልጸዋል።
የዘንድሮው የኢትዮጵያ የሠንደቅ ዓላማ ቀን ክብረ በዓልም የታላቁ ህዳሴ ግድብ በተጠናቀቀ ማግስት መከበሩ ትርጉሙን ከፍተኛ እንደሚያደርገው አስረድተዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ኢሳ ቦሩ፤ ሠንደቅ ዓላማ የአንድ ሀገር የሉዓላዊነት መገለጫ ምልክት ነው ብለዋል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ በተጠናቀቅበት ማግስት የሚከበረው የዘንድሮ የኢትዮጵያ የሠንደቅ ዓላማ ቀንም የአዲሱን ትውልድ ታሪክ ሰሪነት የገለጠ ታላቅ ክብርን የሚያጎናጽፍ ልዩ ክስተት መሆኑን ገልጸዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል መብራቱ አለሙ (ዶ/ር)፤ የዘንድሮው የሠንደቅ ዓላማ ቀን የአሁኑ ትውልድ ህዳሴን በማሳካት ቅድመ አያቶች ለሀገራቸው ክብር በዓድዋ ያስመዘገቡትንና የከፈሉትን ውድ ዋጋ በማሰናሰል የሚከበር መሆኑ ትርጉሙን ከፍ ያደርገዋል ብለዋል።
የሠንደቅ ዓላማ ቀን ሲከበርም ይህን የድል ታሪክና የአሁኑ ትውልድ በላቡ ያስመዘገበውን የህዳሴ ስኬት በማሰብ ማክበር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
የምክር ቤቱ አባላት በማከልም የህዳሴ ግድብ ስኬትም ኢትዮጵያን የአፍሪካ የኃይል ማማ በማድረግ ፍትሀዊ ውሃ ሃብት ተጠቃሚነት ሥርዓትን በመዘርጋት ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስር እንደሚያሳድግ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞም በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ መስክ የዜጎችን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ በተሻለ የማንሰራራት ከፍታ ዕድገት እያስመዘገበ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ምርቃት የተበሰሩ ግዙፍ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች የሀገርን የተረጅነትና ጥገኝነት የኩስመና ታሪክ በመስበር ለኢትዮጵያ ማንሠራራት መሰረት እንደሚሆኑ ተናግረዋል።
ግንባታቸው የተጀመረው የአፈር ማዳበሪያና የተፈጥሮ ጋዝ ማጣሪያ ፋብሪካዎች የሀገርን ከፍተኛ የገንዘብ ወጪ በመቀነስ ለኢትዮጵያ ማንሠራራት ዕይታ ቀያሪ ናቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር ጥያቄ በሰጥቶ መቀበል መርህ የተመሰረተ የትብብር አጀንዳ መሆኑን ተናግረዋል።
የ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት የመንግስት የልማት የትኩረት መስኮች ስኬት በሕግ ማውጣት፣ በክትትል ቁጥጥርና በፓርላማ ዲፕሎማሲ አስፈላጊውን ስራ አንደሚያከናወኑ አብራርተዋል።
የህዳሴ ግድብ ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችም ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ በሚደረገው ጥረት የማይተካ ሚና እንደሚኖራቸው ጠቅሰዋል።