የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ኢትዮጵያ ለያዘችው የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ስኬት ሚናው የላቀ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ኢትዮጵያ ለያዘችው የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ስኬት ሚናው የላቀ ነው

አሶሳ፤ መስከረም 30/2018(ኢዜአ)፦ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ኢትዮጵያ ለያዘችው የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ስኬት ሚናው የላቀ መሆኑን የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም አስታወቀ።
ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ ከተጀመረ ወዲህ እስካሁን 25 ሚሊዮን ዜጎች ምዝገባ ማከናወናቸውን የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም አስታውቋል።
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ እና አስፈላጊነት ዙሪያ የምክክር መድረክ አካሄዷል።
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የምዝገባ ዘርፍ ኃላፊ ሔኖክ ጥላሁን በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ዜጎች ዘርፈ ብዙ አገልግሎትን በተቀላጠፈ እና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ እንዲያገኙ የሚያስችል ነው።
ፕሮግራሙ ከተጀመረ እስከ አሁን ድረስ በሀገር አቀፍ ደረጃ 25 ሚሊዮን ዜጎች ምዝገባ ማከናወናቸውን ጠቅሰው፥ በ2018 በጀት ዓመት 40 ሚሊዮን ዜጎችን ለመመዝገብ ዕቅድ መያዙን ገልጸዋል።
ፋይዳ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ አገልግሎቶችን ለማግኘት የሚያስችልና በህጋዊ መንገድ በኢትዮጵያ የሚኖሩ ስደተኞችንም እንደሚያካትት ኃላፊው ተናግረዋል።
የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ኢትዮጵያ ለያዘችው የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ስኬታማነት ቁልፍ ሚናን የሚጫወት ነው ብለዋል።
ህብረተሰቡ የፋይዳን አስፈላጊነት ተገንዝቦ እንዲመዘገብ የአመራሩ የጋራ ጥረት እንደሚጠበቅም አንስተዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢሳቅ አብዱልቃድር በበኩላቸው፥ ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ የዜጎችን ፍትሀዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ሁሉንም የሚያካትት መርሃግብር መሆኑን ጠቅሰዋል።
ፋይዳ የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚያረጋግጥ የሀገርን ተወዳዳሪነት የሚያሳድግ በመሆኑ መንግስት በትኩረት እየሰራበት ይገኛል ብለዋል።
በክልሉ ሁሉም ዜጎች የዲጂታል መታወቂያ ባለቤት እንዲሆኑ የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመጠቀም እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።
በክልሉ በ2018 በጀት ዓመት ከ355 ሺህ በላይ ዜጎችን የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ባለቤት ለማድረግ መታቀዱም ተገልጿል።
በመድረኩ ላይ የክልል፣የዞን እና የወረዳ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም አጋር አካላቶች ተገኝተዋል።