የመደመር መንግስት መጽሃፍ ሀገርን ለማበልጸግ የሚያግዙ ሃሳቦችን የሚያመላክት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር መንግስት መጽሃፍ ሀገርን ለማበልጸግ የሚያግዙ ሃሳቦችን የሚያመላክት ነው

አዳማ ፤ መስከረም 30/2018(ኢዜአ)፡- የመደመር መንግስት መጽሃፍ አንድነት እና እድገትን አጣምሮ ሀገርን ለማበልጸግ የሚያግዙ መሰረተ ሃሳቦችን የሚያመላክት መሆኑን ምሁራን ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመደመር እሳቤ የጻፉት 4ኛው መጽሐፍ የመደመር መንግሥት ሲመረቅ መጽሐፉ ዛሬ ላይ ሆኖ የተሻለ ነገን የሚያይና የሚገነባ ስለመሆኑ ማንሳታቸው ይታወሳል።
መጽሐፉ መነሻ፣ መዳረሻ፣ መንገድ እና መንግስት በተሰኙ አራት ሐሳቦች ዙሪያ እንደሚያጠነጥን ጠቅሰው ''የመደመር መንግስት የኢትዮጵያን ብልጽግና የሚመኝ ብቻ ሳይሆን እንዲሳካ የሚሰራ ነው'' ብለዋል።
ኢዜአም የመደመር መንግስት መጽሐፍ ለኢትዮጵያ ያለውን ፋይዳ አስመልክቶ ከምሁራን ጋር ቆይታ አድርጓል።
ምሁራኑም መጽሐፉ ኢትዮጵያን በተሻለ መልኩ ለመገንባት መንገድ ቀያሽ እና አቅጣጫ ጠቋሚ መሆኑን አንስተው አንድነት እና እድገትን አጣምሮ ሀገርን ለማበልጸግ የሚያግዙ መሰረተ ሃሳቦችን የሚያመላክት ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት ደመላሽ መንግስቱ (ዶ/ር)፤ መጽሐፉ ሀገርን በተሻለ መልኩ ለመምራት እና ብልጽግናን እውን ለማድረግ የሚያስችሉ አንኳር ሃሳቦችን የያዘ መሆኑን አብራርተዋል።
የመደመር ፍልስፍና ከግለሰብ ተነስቶ ስትራቴጂዎችን እየቀየሰ አሁን የመደመር መንግስት ላይ የደረሰ የፖለቲካ አስተሳሰብና ፍልስፍና መሆኑንም አንስተዋል።
የመደመር መንግስት መጽሐፍ የሀገር እድገትና አንድነትን አጣምሮ የያዘ እና ዜጎችንም ለአንድ ዓላማ እንዲሰለፉ የሚያስችሉ ጠንካራ ሃሳቦችን በስፋት ያነሳ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህም ባለፈ የመደመር መንግስት እይታ ካለፉት ስርዓት ውስጥ ለትውልድ የሚጠቅሙ፣ ሀገር የሚገነቡ እይታዎችን የሰነደ፤ ሀገር አሻጋሪ ሀሳቦች የተካተቱበት መሆኑንም አስረድተዋል።
መጽሐፉ ኢትዮጵያን በተሻለ ደረጃ ለማስቀጠል ያለመ በጥበብ የተደራጀ ነው ያሉት ዶክተር ደመላሽ፤ በተለይም የመንግስት ሃላፊነት ላይ ያሉ ሁሉ የመፅሃፉን ይዘት በአግባቡ በመረዳት ለሀገርና ለህዝብ መስራት አለባቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት ዮሐንስ በንቲ (ዶ/ር) በበኩላቸው የመደመር መንግስት መጽሐፍ ከግለሰብ የተሻገረ፤ ለሀገር ግንባታ የሚጠቅም እይታና ፍልስፍና የያዘ መሆኑን ተናግረዋል።
መጽሐፉ በምሁራዊ እሳቤ ሀገርን እንዴት መምራት እንደሚቻልና መዳረሻ ግብን በግልጽ ያስቀመጠ እንዲሁም ተቃርኖዎችን በምን መልኩ አስታርቆ ብልጽግና ማረጋገጥ እንደሚቻል በግልጽ ያስቀመጠ ነው ብለዋል።
መጽሀፉ በተለይ ለትምህርት ማህበረሰብ እንዲሁም ለተመራማሪዎች ትልቅ እድል መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህ መልኩ በተሰነደ ሀሳብ ሀገርን በመምራት በአጭር ጊዜ ልማትን ለማረጋገጥ የሚረዳ መሆኑን ገልጸዋል።