ሰላም ፀንቶ ሰፋፊ የልማት ስራዎች ዳር እንዲደርሱ የበኩላችንን እንወጣለን - ኢዜአ አማርኛ
ሰላም ፀንቶ ሰፋፊ የልማት ስራዎች ዳር እንዲደርሱ የበኩላችንን እንወጣለን

ደሴ፤ መስከረም 30/2018 (ኢዜአ)፡- በመንግስት የትኩረት አቅጣጫ መሰረት ሰላምን በማፅናት ሰፋፊ የልማት ስራዎች ከዳር እንዲደርሱ የበኩላቸውን እንደሚወጡ በደቡብ ወሎ ዞን ደሴ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ መስከረም 26/2018 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮችና የፌደሬሽን ምክር ቤት የ2018 የስራ ዘመን የጋራ የመክፈቻ ላይ ንግግር ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።
ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው ከነሷቸው ዋና ዋና ነጥቦች መካከል በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማት፣ በዓባይና በቀይ ባሕር ላይ ያተኮሩ ዲፕሎማሲያዊና ሰላማዊ ጥረቶችን አጠናክሮ ስለማስቀጠል፣የዲጂታል አገልግሎትን ማስፋት እና የተለያዩ ግዙፍ የግንባታ ፕሮጀክቶች ይገኙበታል፡፡
በእነዚህና በሌሎችም የመንግስት የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ኢዜአ የደሴ ከተማ ነዋሪዎችን አነጋግሯል።
ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ አንዳርጌ ስመኝ በሰጡት አስተያየት፤መንግስት በሀገሪቱ ሰላምን ለማፅናት የሰጠው ትኩረት የሚበረታታና ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንደሚደግፉ ተናግረዋል።
በተጨማሪም የተጀመሩ ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ መገለጹ የኢትዮጵያን ሁለተናዊ እድገት ለማረጋገጥ ያስችላል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል።
በተለይ የተፈጥሮ ጋዝ፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የባሕር በር፣ የቱሪዝም ልማትና ሌሎች ፕሮጀክቶች ትውልድን ታሳቢ ያደረጉ በመሆናቸው የሚደነቁ ናቸው፤ ለውጤታማነታቸውም የድርሻችንን እንወጣለን ብለዋል።
ወይዘሮ የመንዝወርቅ ታደሰ በበኩላቸው፤ በኢትየጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና አንድነትን ለማጠናከር መንግስት የሰጠው ትኩረት የሚበረታታና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ሰላሙን ለማጽናት ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን የሀገርና የዜጎችን ተጠቃሚነት ማሳደግ ለሚያስችሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ግንባታ ትኩረት መሰጠቱን እንደሚደግፉት ተናግረዋል።ከመንግስት ጎን ተሰልፈን ሰላማችንና ልማታችንን እናረጋግጣለን ብለዋል።
እድገታችንን እና ሰላማችንን በማይፈልጉ የውጭ ጠላቶች እኩይ ሴራ ሳንበገር የሕዳሴውን ግድብ በማስመረቃችን ተደስተናል ያሉት ደግሞ ወይዘሮ አረጋሽ ጌታሁን ናቸው።
ይህም በሀገራዊ ጉዳዮች፣ ብሔራዊ ፕሮጀክቶችና ጥቅሞቻችን ላይ ድርድር የሌለን መሆኑን ያረጋገጥንበትና ለወደፊትም ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ከመንግስት ጎን ተሰልፈን የተጀመሩ ልማቶችንና ሰላማችንን በአንድነት ለማስጠበቅ በያለንበት የበኩላችንን እንወጣለን ብለዋል።
የመንግስት የ2018 ስራ ዘመን የትኩረት አቅጣጫም ኢትዮጵያ የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ የሚያሳልጥና መሰረት የሚጥል መሆኑን ተገንዝበናል ሲሉ አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል።