ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር ) በሀዲያ እና ስልጤ ዞኖች የተገነቡ የሞዴል የገጠር መንደሮችን አስረከቡ - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር ) በሀዲያ እና ስልጤ ዞኖች የተገነቡ የሞዴል የገጠር መንደሮችን አስረከቡ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 30/2018 (ኢዜአ)- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር ) በሀዲያ እና ስልጤ ዞኖች የተገነቡ የሞዴል የገጠር መንደሮችን ዛሬ አስረክበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር ) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ረቡዕ በሀላባ እና ከምባታ ዞኖች የነበረውን የሞዴል የገጠር መንደሮች ርክክብ ሥነሥርዓት በመቀጠል ዛሬም በሀዲያ እና ስልጤ ዞኖች የተገነቡ መንደሮች ማስረከባቸውን ገልጸዋል።
መንደሮቹ ባለ ሶስት መኝታ ቤት መኖሪያዎች ለማብሰል የሚያገለግል የባዮጋዝ መሣሪያ፣ የፀኃይ ኃይል ማመንጫ፣ የዶሮ ማርቢያ፣ የተለየ የእንስሳት በረት የተሟላላቸው መሆኑን ጠቁመዋል።
በተመጣጣኝ አነስተኛ ወጪ ከአካባቢ በሚገኙ ግብዓቶች የተሻለ መኖሪያ ከማስገኘት አንፃር ለገጠሩ ማኅበረሰብ ብልጽግና ያለንን ሕልም የሚያሳይ ነው ብለዋል።
እንደ ማኅበረሰብ አዲስ ሀሳቦች ሲፈልቁ “አይቻልም” በሚለው የቆየ አስተሳሰብ የመፈተን ተግዳሮት ይደቀንብን ይሆናል። ይሁንና በተጨባጭ በሚታየውና በተገኘ ውጤት ላይ ወደ አለማመን እና አለመቀበል በሚመራን የሀሳብ ወጥመድ ውስጥ መውደቅ የለብንም ሲሉ ገልጸዋል።
ዜጎች ለውጥ እንደሚቻል ሀብቶቻችንን ወደ ትክክለኛ የቅድሚያ ትኩረቶቻችን ካዋልንም ማኅበረሰብን በርግጥም ማሻገር እንደምንችል ማመን እንደሚገባቸውም ነው የተናገሩት።
በአራቱ ዞኖች የተሠራው ሥራ በመላው ክልሉ መደገም ይኖርበታል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የክልሉ አመራር ይኽን ታላቅ ስራ ይፈጽማሉ ብለው እንደሚያምኑም አመልክተዋል።