በፕሬዝዳንቱ የቀረቡ የመንግስት የትኩረት አቅጣጫዎች ለሀገራዊ ልማትና ማንሰራራት መሰረት የሚያኖሩ ናቸው- ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
በፕሬዝዳንቱ የቀረቡ የመንግስት የትኩረት አቅጣጫዎች ለሀገራዊ ልማትና ማንሰራራት መሰረት የሚያኖሩ ናቸው- ምሁራን

ወልቂጤ፤ መስከረም 30/2018 (ኢዜአ)፡- በኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ የቀረቡ የመንግስት የትኩረት አቅጣጫዎች ለሀገራዊ ልማትና ማንሰራራት መሰረት የሚያኖሩ መሆናቸውን የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።
ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ የመንግስትን እቅዶችና ልዩ የትኩረት አቅጣጫዎች ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡
በፕሬዝዳንቱ የቀረቡ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫዎችን በተመለከተ ኢዜአ በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ ምሁራንን አነጋግሯል።
ምሁራኑም በማብራሪያቸው በፕሬዝዳንቱ የቀረቡ የመንግስት የትኩረት አቅጣጫዎች ለሀገራዊ ልማትና ማንሰራራት መሰረት የሚያኖሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ተመራማሪና መምህር በቃሉ ዋቺሶ፤ በሁለቱ ምክር ቤቶች መክፈቻ ላይ በፕሬዝዳንቱ የቀረቡት ጉዳዮች የሀገርን ልማትና ማንሰራራት እንዲሁም የዓለምን ነባራዊ እውነታዎች መሰረት ያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በሁሉም ዘርፎች የተጀመሩ ስራዎችና የተነሱ እቅዶች ሀገርን የሚለውጡ እና ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ በጋራ ልንተጋ ይገባል ብለዋል።
በዩኒቨርሲቲው የመልካም አስተዳደርና ልማት መምህር አዳፍረው አዳነ፤ የህዳሴ ግድቡ እውን በሆነበት አግባብ እንደ የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካና የተፈጥሮ ጋዝ ምርት ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም ለማሳካት የተጀመረው ጥረትም ኢኮኖሚውን ከውጭ ጫና ለማላቀቅ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የማስከበርና የዜጎችን ክብር የማስጠበቅ ጉዳይ የዲፕሎማሲ ማጠንጠኛ ሆኖ መወሰዱም የሚደነቅ ስለመሆኑ አንስተዋል።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሥራን ጨምሮ መንግስት ለውይይትና እርቅ ያሳየው ቁርጠኝነት በሁሉም ወገን ተቀባይነት ሊኖረው ይገባል ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ዲንና የህግ መምህር ወልደማርያም ቀነኒሳ ናቸው፡፡
ለተቋማዊ ጥንካሬና ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ የተሰጠው ትኩረትም የኢትዮጵያን እድገትና ብልጽግና ለማሳካት ወሳኝ መሆኑንም ገልጸዋል።