ቀጥታ፡

ክልሉ የተደራጁ ወንጀሎችንና የፀረ-ሰላም ኃይሎችን እንቅስቃሴ በቀላሉ ለመከላከል የሚያስችል አቅም አሳድጓል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 30/2018 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል የተደራጁ ወንጀሎችንና የፀረ-ሰላም ኃይሎችን እንቅስቃሴ በቀላሉ ለመከላከል የሚያስችል አቅም ማደጉን የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ዘላለም መንግስቴ(ዶ/ር) ገለጹ።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ዘላለም መንግስቴ(ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ የክልሉ ፖሊስ የሕግ ማስከበር አቅሙን ለማጠናከር እና ለህዝብ የሚሰጠውን አገልግሎት ለማሻሻል ሁለንተናዊ ሪፎርም አድርጓል።

ሪፎርሙ የፖሊስን ተቋማዊ አቅም በማጠናከር ለህዝብ የሚሰጠውን የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ለማሻሻል ያለመ መሆኑን ተናግረው፤ ይህ ፖሊስ እንደ ህዝባዊ ተቋም ውጤታማ የሕግ ማስከበር ስራ እንዲያከናውን ያስችለዋል ነው ያሉት።

የፖሊስ ሥራዎችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመደገፍ የአገልግሎት አሰጣጡን ፈጣንና ግልጽ ለማድረግ የዲጂታል ለውጥ ሥራዎች ማድረጉንም ኮሚሽነሩ ጠቅሰዋል።

የፖሊስ መዋቅርን በማዘመን የሰው ኃይል ምደባን በተዘጋጀ መመሪያና ስታንዳርድ መሠረት መዋቀሩን ነው ያስረዱት።

ገለልተኛ የፖሊስ አገልግሎት እና የሕዝብን አመኔታ እና ፍትሕን የማስፈን አቅምን ማጠናከር ላይ ትኩረት ተደርጓል ሲሉም አብራርተዋል።

ተቋማዊ ሪፎርሙ በክልሉ የተደራጁ ወንጀሎችንና የፀረ-ሰላም ኃይሎችን እንቅስቃሴ በቀላሉ ለመከላከል የሚያስችል አቅም እያሳደገ እንደሆነ አስታውቀዋል።

በዚህም በክልሉ ሰላም እየሰፈነ መምጣቱን ተናግረው፤ አሁን ላይ በክልሉ የልማት ተግባራትን ጨምሮ የመማር ማስተማር ስራዎችን በተረጋጋ ሁኔታ ለማከናወን መቻሉን ተናግረዋል።

ለአርሶ አደሩ የግብርና ግብዓቶች በአግባቡ ተደራሽ በመሆናቸው የእርሻ ሥራው በተረጋጋ ሁኔታ መከናወን መቻሉን ገልፀዋል።

በክልሉ አስተማማኝ ሰላም ለማረጋገጥ የክልሉ የፀጥታ ምክር ቤት ስልታዊ አቅጣጫ ማሰቀመጡን ተናግረዋል።

በዚህም የክልሉ የፀጥታ መዋቅር ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ዘላለም መንግስቴ(ዶ/ር) አስታውቀዋል።

በክልሉ የውጭ ጠላት ተልዕኮን አንግበው የሚንቀሳቀሱ ባንዳዎችን የማፅዳት ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም