ቀጥታ፡

ለሰንደቅ ዓላማችን ክብርና ለሀገራችን ሰላም በፅናት  ቆመናል - የመከላከያ ሰራዊት አባላት

ጅማ፤ መስከረም 30/2018(ኢዜአ) ፡- የነጻነት፣ የጀግንነትና የአንድነታችን ምልክት ለሆነው ሰንደቅ ዓላማችን ክብርና ለሀገራችን ሰላም በፅናት ቆመናል ሲሉ በመከላከያ  የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ የሰራዊት አባላት ገለጹ።

የዳሎል ማዕከላዊ እዝ የሰራዊት አባላት ጥቅምት 3 /2018 ዓ.ም የሚከበረውን የሰንደቅ ዓላማ  ቀንን በማስመልከት ከኢዜአ ጋር  ቆይታ አድረገዋል።

አባላቱ፤  የነጻነት፣ የጀግንነትና የአንድነታችን ምልክት ለሆነው ሰንደቅ ዓላማችን ክብርና ለሀገራችን ሰላም ቁርጠኛ በመሆን በፅናት  ቆመናል ሲሉ ተናግረዋል። 

ከአባላቱ መካከል ሻለቃ ጌታይመስገን ገዛኸኝ ፤  ሰንደቅ አላማችን የሀገራችን ነጻነትና አንድነት ብሎም የጀግንነታችን ምልክት ነው ሲሉ ገልጸዋል። 

ውትድርና ለሀገር ፍቅር እና ለሰንደቅ ዓላማ ክብር የተለየ ስሜት ያለው ሙያ መሆኑን አንስተው፤ የሰንደቅ ዓላማ ቀንን በሀገር ፍቅር ስሜት ሆነው በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚያከብሩት ተናግረዋል።

አባቶቻችን በአኩሪ ገድል ያቆዩልንን ሀገር እኛም ክብሯንና አንድነቷን ጠብቀን ለማቆየት ተግተን እንሰራለን ያሉት ደግሞ ሌላኛው የሰራዊቱ አባል ሻለቃ ይርጋለም ገብረ ህይወት ናቸው።

ሀገራችን በታሪኳ ተደጋጋሚ የውጭ ወራሪ የገጠማት ቢሆንም በተባበረ ክንድና በጀግንነት በመመከት መቀልበስ እንደቻለችም አውስተዋል።

ዛሬም በየትኛውም በኩል በሀገራችን ላይ የሚሰነዘረውን ትንኮሳ ለመመከት እና ጠላትን ለማሳፈር በሙሉ ዝግጁነት ላይ እንገኛለን ብለዋል።

የዳሎል ማእከላዊ ዕዝ ጁኒየር ዋራንት ኦፊሰር ሚሊሻ በቀለ በበኩላቸው፤  ሰንደቅ ዓላማ ለሀገር ክብርና ፍቅር የተከፈለ መስዋዕትነትን የምናስታውስበት ምልክት ነው ብለዋል።

ወታደር በመስዋዕትነት ለሰንደቁ ይወድቃል፤ ሲሰዋም ለሀገሩ ሰላምና ለሰንደቅ ዓላማው ክብር በጀግንነት ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ሰንደቅ ዓላማችን ሀገራችን የምትወከልበት፤ የኢትዮጵያ ማንነት የሚገለጽበት በመሆኑ ቀኑን በተለያዩ ዝግጅቶች እናከብራለን  ብለዋል።

የሰራዊቱ አባላት የነጻነት ሰንደቅ ዓላማችን የጀግንነትና የአንድነታችን ምልክት፤ የሀገራችንን ክብርና ሰላም ለማስከበር ያለንን ፅናት፣ ተልዕኮና ቁርጠኝነት የምናሳይበትም ነው ሲሉ ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም