ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ በእውቀት እና ክህሎት የሚመራ ሰራዊት በመገንባት ሂደት ውስጥ ገንቢ ሚና እየተወጣ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 29/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ በእውቀት እና ክህሎት የሚመራ ሰራዊት በመገንባት ሂደት ውስጥ ገንቢ ሚና እየተወጣ መሆኑን በዩኒቨርሲቲው የምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ኮሎኔል ሚኒሊክ ዋለ (ዶ/ር) ገለጹ። 

የአህጉሪቷን ሰላም እና ደህንነት ማስከበር የሚያስችል የሰው ሀይል እያፈራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ የምርምር አስተዳደርን፣ ፈጠራንና የማኅበረሰብ ተሳትፎን ማጎልበት ላይ ያተኮረ የሁለት ቀናት አውደ ጥናት ማካሄድ ጀምሯል።


 

ዓላማውም ከተለያዩ ተቋማት የመጡ አመራሮች እና ሙያተኞች በምርምር፣ በፈጠራ፣ በማህበረሰብ ግልጋሎት እና በቴክኖለጂ ሽግግር ላይ ያላቸውን ተሞክሮ ለዩንቨርሲቲው እንዲያካፍሉ ማስቻል ነው።

የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ኮሎኔል ሚኒሊክ ዋለ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የሰራዊቱን የመፈጸም አቅም ለማሳደግ ምርምር ወሳኝ ነው።

ከዚህ አኳያ ዩንቨርሲቲው በተሰጠው ተልዕኮ በእውቀት እና ክህሎት የሚመራ ሰራዊት በመገንባት ሂደት ውስጥ ገንቢ ሚና እየተወጣ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ዩንቨርሲቲው ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ተማሪዎችን በመቀበል እያስተማረ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ከዩንቨርሲቲው የወጡ ምሩቃን አገራቸውን በተለያየ የአመራር ደረጃ እያገለገሉ እንደሚገኙ ገልጸው፤ ይህም ኢትዮጵያ ከሀገራት ጋር በጋራ ለማደግ እና ደህንነትን ለማስከበር ያላትን ጽኑ አቋም የሚያሳይ መሆኑን አስታውቀዋል።

እነዚህ ተግባራት የኢትዮጵያን ስም በአፍሪካ ውስጥ ከፍ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

በመከላከያ ዋር ኮሌጅ የስትራቴጂያዊ ጥናት ኢንስቲቲዩት ዲን ስራው ደማስ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ መከላከያ በርካታ የትምህርት እና የምርምር መሰረተ ልማቶችን የያዘ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል።

ስልጠናው እነዚህን ሀብቶች እንዴት በጋራ መጠቀም እንደሚቻል ግንዛቤ የሚፈጥር መሆኑን አመልክተዋል።

በተጨማሪ የምርምር ፐሮጀክቶችን በጀት እንዴት መጠቀም እና ማፈላለግ እንደሚቻል ትምህርት ያገኙበት መሆኑን ጠቁመዋል። 

አውደ ጥናቱ አጋዥ የሆኑ የምርምር ውጤቶችን ከማውጣት አኳያ የትኩረት አቅጣጫዎችን ያመላከተ መሆኑን በኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስ እና ማህበራዊ ጥናት ኮሌጅ ዲን አይችሉም ከተማ (ዶ/ር) አስታውቀዋል።

በተለይም በበጀት አጠቃቀም እና በፋይናንስ ምንጭ ላይ ግንዛቤ የተገኘበት መሆኑን አመልክተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም