ቀጥታ፡

ኢንስቲትዩቱ በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ለመጀመሪያ ጊዜ በሶስተኛ ዲግሪ ስልጠና ሊጀምር ነው

አዲስ አበባ፤መስከረም 29/2018(ኢዜአ)፦የፌደራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ለመጀመሪያ ጊዜ በሶስተኛ ዲግሪ በሁለት ፕሮግራሞች ስልጠና ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ በ2018 የትምህርት ዘመን አዲስ የሚጀመሩ መርሃ ግብሮችን አስመልክቶ የተዘጋጀውን የመረጃ ሳምንት በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።


 

የፌደራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር ( ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ኢንስቲትዩቱ የገበያውን ፍላጎትና የሰልጣኞችን አማራጭ ለማስፋት እየሰራ ይገኛል።

በዚሁ መሰረት ኢንስቲትዩቱ የገበያውን ፍላጎትን መሰረት ያደረጉና የእሴት ሰንሰለት የተሰራላቸውን 11 አዳዲስ የስልጠና ፕሮግራሞች እንደሚጀምር አስታውቀዋል።

በ2017 በጸደቀው የትምህርትና ስልጠና የብቃት ማረጋገጫ ማዕቀፍ መሰረት ደረጃ 6 የመጀመሪያ ዲግሪ፣ ደረጃ 7 ሁለተኛ ዲግሪ እንዲሁም ደረጃ 8 ሶስተኛ ዲግሪ መሆኑን አብራርተዋል።

በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ለመጀመሪያ ጊዜ በሶስተኛ ዲግሪ በሁለት ፕሮግራሞች፣በቅድመና ድህረ ምረቃ ዘጠኝ ፕሮግራሞች ለመጀመር ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

ኢንስቲትዩቱ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና አገራት ያለውን ትስስር ለማጠናከር በየአመቱ እስከ 250 ለሚደርሱ የጎረቤት አገራት ዜጎች የስልጠና እድል እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሰልጣኞች በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ ከአለም አቀፍ ተቋማት ጋርም በጥምር ዲግሪ መርሃ ግብር በትብብር እንደሚሰራም ገልጸዋል።

የኢንስቲትዩቱ የመግቢያ የመቁረጫ ነጥብ የተማሪዎች የመቀበያ መስፈርት በተመለከተም በቅርቡ መረጃ ይፋ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

ኢንስቲትዩቱ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በ16 የስልጠና ተቋማት ተደራሽ ለመሆን እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም