ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ቤልጄም የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ትብብራቸውን አጠናክረው ይቀጥላሉ -አምባሳደር ሀደራ አበራ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 29/2018 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያና ቤልጄም በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን ጉዳዮች ያላቸውን ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሀደራ አበራ ገለጹ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሀደራ አበራ በቤልጄም የውጭ የጉዳይ ሚኒስቴር የውጭ ንግድና ልማት ትብብር ዋና ጸሀፊ እና የዳይሬክተሮች ቦርድ ፕሬዝዳንት ቴወዶራ ገንትዚስ ከሚመራ ልዑክ ጋር በሁለቱ ሀገሮች ዙሪያ ፖለቲካዊ ምክክር አድርገዋል፡፡


 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሀደራ አበራ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያና ቤልጄም በሁለትዮሽ እና በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ የረጅም ዘመን አጋርነት አላቸው፡፡

የኢትዮጵያና ቤልጄም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመረው እ.አ.አ በ1906 እንደነበር አስታውሰው በመጪው የፈረንጆቹ ዓመት 120ኛ ዓመታቸውን በጋራ ያከብራሉ ብለዋል፡፡

በሁለቱ ሀራት መካከል ያለውን ወሳኝ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር በቀጣናዊ፣ የሁለትዮሽ እና ባለብዙወገን ጉዳዮች ላይ ተቋማዊ ትብብርን የሚፈጥር የመግባቢያ ስምምነት በቅርቡ እንደሚፈራረሙም ገልጸዋል፡፡

የፖለቲካ ምክክሮች ከሁለትዮሸ ባለፈ በአፍሪካ ህብረትና በአውሮፓ ህብረት ባሉ ባለብዙ ወገን የውጭ ግንኙነቶች ላይ በትብብር መሥራት ያስችላል ብለዋል፡፡

ቤልጄም የኢትዮጵያ የልማት አጋር መሆኗን የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የልማት ትብብርና የነፃ የትምህርት ዕድል ጉልህ ሚና እንዳላት ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የቤልጄም ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ተሳትፎ እያደገ መምጣቱን ገልጸው፤ በግብርና፣ በአረንጓዴ ኃይል፣ ሎጂስቲክስ እና አምራች ዘርፍ ተሳትፏቸውን እንዲያሳድጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ኢትዮጵያ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ የሚያሳደግ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ገቢራዊ ማድረጓን አንስተው፤ ለዚህ ጥረት መሳካት የአየር ትራንስፖርት ትስስር እንዲያድግ እናደርጋለን ብለዋል፡፡

ቤልጄም የኢትዮጵያን ቡና በከፍተኛ መጠን ከሚገዙ ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን በማንሳት፤ የአውሮፓ ህብረት በመጪው ታህሳስ ወር ገቢራዊ በሚያደርገው "የአውሮፓ ህብረት ደን ጭፍጨፋ ደንብ" አጋርነቷን እንደምታሳይ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡


 

በቤልጄም የውጭ የጉዳይ ሚኒስቴር የወጪ ንግድና ልማት ትብብር ዋና ጸሀፊ እና የዳይሬክተሮች ቦርድ ፕሬዝዳንት ቴወዶራ ገንትዚስ በበኩላቸው ሁለቱ ሀገራት ከሁለትዮሽ ባለፈ በባለብዙ ወገን ተቋማት ከሊግ ኦፍ ኔሽን ምስረታ ጀምሮ የረጅም ዘመን ግንኙነት አላቸው ብለዋል፡፡

የአፍሪካ ድምጽ በዓለም አቀፍ መድረክ መደመጥ እንዳለበት በመጥቀስ፤ ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ የልብ ምት መሆኗን አረጋግጠዋል፡፡

ኢትዮጵያ አስደናቂ የኢኮኖሚ ሪፎርም ማድረጓን ገልጸው፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የኢኮኖሚ ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

የቤልጄም ተመራማሪዎችና መምህራን በኢትዮጵያ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች እንደሚገኙ በመጥቀስ፤ ለኢትዮጵያውያን የሚሰጠው የትምህርት ዕድል ቀጣይነት ይኖረዋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም