ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የባቡር ፕሮጀክትን በራስ አቅም መገንባት መጀመሯ የማንሰራራት ጉዞዋ ማሳያ ነው -ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ መስከረም 29/2018(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ የባቡር ፕሮጀክትን በራስ አቅም መገንባት መጀመሯ የማንሰራራት ጉዞዋ  ማሳያ ነው ሲሉ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለጹ።   

ኤ ኤም ጂ ኢንዱስትሪ ፓርክን ከዋናው ኢትዮ-ጁቡቲ ባቡር መስመር ጋር የሚያገናኝ የባቡር  ሃዲድ ግንባታ ዛሬ ተጀምሯል። 

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)  የፕሮጀክቱን ግንባታ ማስጀመሪያ የመሰረት ድንጋይ ከሌሎች የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን አስቀምጠዋል፡፡   


 

የባቡር መስመር ግንባታው መሉ በሙሉ በኢትዮ-ጁቡቲ ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ባለሙያዎች የሚገነባ ሲሆን፤ በስድስት ወራት  ለማጠናቀቅ  መታቀዱ ተገልጿል።  

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ አህጉራዊ  ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት መተግበር ጀምራለች።     

ቀጣናዊ  ኢኮኖሚ ትስስር  ያለመሰረተ  ልማት  ግንባታ  የሚታሰብ አይደለም  ያሉት  ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ  ለባቡር  መሰረተ  ልማት ግንባታ  ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።     

የኤ ኤም ጂ ኢንዱስሪ ፓርክን ከዋናው ኢትዮ-ጁቡቲ ባቡር መስመር ጋር የሚያገናኘው የግንባታ ፕሮጀክት የዚሁ  አካል መሆኑን ተናግረዋል።  

ግንባታው ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ  አቅም  እንደሚካሄድ ጠቁመው፤ ኢትዮጵያ በራስ አቅም ብልፅግናዋን የማረጋገጥ  ውጥኗ ፍሬ  እያፈራ ለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል። 

ይህም የኢትዮጵያ የማንሰራራት ጉዞ አመላካች ነው ሲሉም ገልጸዋል። 

ኢትዮጵያ በአፍሪካ የኢኮኖሚ ትስስር ውስጥ ጉልህ ሚና መጫወት አለባት ያሉት ሚኒስትሩ፤ ለዚህም ለመሰረተ ልማት መስፋፋት ትኩረት መስጠቷን አስረድተዋል።


 

የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር  ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ታከለ ዑማ በበኩላቸው፤ የባቡር  ሃዲድ ግንባታውን  ከዲዛይን  ጀምሮ  በውስጥ አቅም ለማካሄድ  ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።    

አክሲዮን ማህበሩ የሎጂስቲክስ አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ የባቡር መስመር፣ የፈጣን መንገድ እና የሌሎች መሰረተ  ልማት ግንባታዎችን በስፋት ለማካሄድ ግብ መያዙንም አብራርተዋል።    

የኤ ኤም ጂ ሆልዲንግስ ባለቤትና ሥራ አስፈጻሚ አብዱልሃኪም መሀመድ እንዳሉት፤ ፕሮጀክቱ ወደ ኢንዱስትሪው የሚገባውን ጥሬ ዕቃ  እና ከኢንዱስትሪ ፓርኩ የሚወጣውን ምርት ለማሳለጥ ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል።          

የወጪ ንግድን ለማበረታታት እና የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚው ውስጥ የጎላ ሚና እንዲጫወት በመንግሥት እየተዘረጉ ያሉ ማበረታቻዎች የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ የሚያሳድጉ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።   

ድርጅቱ የባቡር ሃዲድ ግንባታውን ለማስጀመር ከኢትዮ ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ጋር ስምምነት ፈጽሞ ወደ ሥራ መግባቱን ጠቅሰዋል፡፡

የፕሮጀክቱ እውን መሆን ሎጂስቲክስን ለማቀላጠፍና ወጪን ለመቀነስ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው አስረድተዋል።  

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም