ቀጥታ፡

ሰላምን በዘላቂነት ለማስጠበቅ የምክር ቤቱ አባላት ክትትልና ድጋፋቸውን ማጠናከር አለባቸው - አፈ ጉባዔ ኢትዮጲስ አያሌው

ወልዲያ፤ መስከረም 29/2018 (ኢዜአ)፡- የከተማዋንና የአካባቢውን ሰላም በዘላቂነት ለማስጠበቅ የምክር ቤቱ አባላት ድጋፍና ክትትላቸውን ይበልጥ ማጠናከር እንዳለባቸው የወልዲያ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ኢትዮጲስ አያሌው አስገነዘቡ ። 

የወልዲያ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት 17ኛ አስቸኳይ ጉባዔ እየተካሄደ ነው። 


 

በጉባዔው መድረክ የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ  አቶ ኢትዮጲስ እንደገለጹት፤ የአካባቢውን ሰላም በዘላቂነት በማስቀጠል የሕዝብን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የምክር ቤቱ አባላት ድጋፍና ክትትላቸውን ይበልጥ ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል።

በተለይ ከወከላቸው ህዝብ ጋር በየጊዜው ተገናኝቶ በመወያየትና በመምከር ሕዝቡ ከመንግስት ጎን በመቆም ሰላሙን በዘላቂነት እንዲያፀና  ድጋፋቸውን ማጎልበት እንዳለባቸው አሳስበዋል። 

የወልዲያ ከተማና አካባቢው ነዋሪ ሰላምን አጥብቆ ይሻል ያሉት አፈ ጉባዔው፣ ለዚህም በየአካባቢው ሕብረተሰቡን ያሳተፈ ቅንጅታዊ ሥራ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።

ችግርን በመቋቋም በወልዲያ ከተማ ኮሪደርን ጨምሮ የተለያዩ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰው፤  የምክር ቤቱ አባላት የወከላቸውን ሕብረተሰብ በማስተባበር ልማቱን የማስቀጠል ሚናቸውን ይበልጥ መወጣት እንዳላባቸው አስገንዝበዋል። 

ሕብረተሰቡ ለሚያነሳቸው የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች አስፈጻሚ አካሉ ምላሽ በመስጠት ሕዝባዊ እርካታን ለማረጋገጥ ክትትሉና ድጋፉን ይበልጥ ማጠናከር  እንዳለባቸውም ገልጸዋል።

እንደ ምክር ቤት አባልነት ሕዝባዊ ውክልናችንን ተጠቅመን ሰላምን በዘላቂነት ለማፅናት ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ያሉት የምክር ቤቱ አባል ደግሞ አቶ ፍስሃ መንግስቴ ናቸው።

ሌላው የምክር ቤት አባል አቶ አሻግሬ ሲሳይ፤  በአካባቢው የሚከናወኑ የልማት ሥራዎችን ስኬታማ በማድረግ ከድህነት ለመውጣት የክትትልና ቁጥጥር ሥራችንን እናጠናክራለን ሲሉ ገልጸዋል።

ምክር ቤቱ በነገው እለትም ቀጥሎ የሚውል ሲሆን የ2018 የበጀት ዓመት የልማትና የፋይናንስ እቅዶች ላይ በመምከር ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም