በባሌ ሮቤ ከተማ የላቀ ውጤት ላመጡ ተማሪዎችና ትምህርት ቤቶች የእውቅናና የገንዘብ ሽልማት ተሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
በባሌ ሮቤ ከተማ የላቀ ውጤት ላመጡ ተማሪዎችና ትምህርት ቤቶች የእውቅናና የገንዘብ ሽልማት ተሰጠ

ሮቤ፤ መስከረም 29/2018 (ኢዜአ)፡-በባሌ ዞን ሮቤ ከተማ አስተዳደር በ2017 ሀገር አቀፍ ፈተና የላቀ ውጤት ላመጡ ተማሪዎችና ትምህርት ቤቶች የእውቅናና የገንዘብ ሽልማት ተሰጠ፡፡
ሽልማቱ ለላቀ ትጋትና ሥራ እንደሚያነሳሳቸው ተሸላሚ ተማሪዎችና የትምህርት ቤት ተወካዮች ገልጸዋል።
እውቅናና ሽልማቱን ያገኙት በ2017 ዓ.ም በ6ኛ እና በ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተናዎች እንዲሁም በሀገር አቀፍ በተሰጠው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች መሆኑም ተመላክቷል።
የሮቤ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሾላዬ ተገኔ እንዳሉት ከተማ አስተዳደሩ እውቅናና ሽልማት የሰጠው በ2017 ዓ.ም በተሰጡ ክልላዊና ሀገር አቀፍ ፈተናዎች ከፍተኛ ውጤት ላመጡ 17 ተማሪዎች ነው።
ከተሸላሚዎች መካከል በአገር አቀፍ ደረጃ 592 ነጥብ በማምጣት የመጀመሪያና ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገባው ተማሪ ካሊድ በሽር እንደሚገኝበት ተናግረዋል።
አስተዳደሩ ከፍተኛውን ውጤት ላስመዘገባው ተማሪ ካሊድ በሽር የ150 ሺህ ብርና የእጅ ስልክ ያበረከተ ሲሆን ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃ ለያዙ ተማሪዎች ደግሞ የ50 ሺህ ብርና የስማርት ስልክ በነፍስ ወከፍ መሸለሙን ገልጸዋል።
የተቀሩት ተማሪዎች እንዳገኙት ውጤት ለትምህርት መርጃ የሚውሉ ቁሶችና የዕውቅናና የምስክር ወረቀት ማግኘታቸውንም አክልዋል።
ሽልማቱን ያበረከቱት የሮቤ ከተማ ከንቲባ አቶ ዲኖ አሚን በበኩላቸው "የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ በሚፈለገው መጠን ባልተሟላበት ሁኔታ የተመዘገበው የተማሪዎች ውጤት የሚያኮራ ነው" ብለዋል፡፡
በሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል ፈተና ከፍተኛ ነጥብ ያስመዘገቡ ተማሪዎች በቀጣይ ለተሻለ ውጤት በርትተው እንዲሰሩም መክረዋል፡፡
ከተሸላሚዎች መካከል በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና 570 በማምጣት የ50ሺህ ብር እና የሞባይል ስልክ የተሸለመችው ተማሪ ቢፍቱ ኑረዲን በሰጠችው አስተያየት ሽልማቱ ለላቀ ትጋት እንደሚያነሳሳት ተናግራለች።
ውጤታማ ሥራ ያከናወኑ ትምህርት ቤቶች፣ መምህራንና የትምህርት ባለድርሻ አካላትን ያመሰገኑት ከንቲባው ለውጤታማ ተማሪዎች የሚሰጠው እውቅናና የማበረታቻ ሽልማት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡