ቀጥታ፡

ከተሽከርካሪ የሚወጣውን የበካይ ጋዝ ልቀት ለመከላከል የሚረዱ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 29/2018(ኢዜአ)፦ከተሽከርካሪ በሚለቀቅ ጭስ የሚከሰተውን የበካይ ጋዝ ልቀት ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው በአገር አቀፍ ደረጃ የወጣውን የተሽከርካሪ በካይ ጋዝ ልቀት መጠን ደረጃ እና የአፈጻጸም መመሪያ  ተግባራዊ  ለማድረግ የሚያግዘውን የግንዛቤ ማስጨበጫ ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት ዛሬ ሰጥቷል።


 

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ሃላፊ ያብባል አዲስ በመርሃ ግብሩ ላይ የተሽከርካሪዎች ለረጅም ጊዜ አገልግሎት መስጠት፣ በቴክኖሎጂ አለመዘመን እና ከነዳጅ አይነቶች ጋር ያሉ ማነቆዎች ለችግሩ ተጠቃሽ መሆናቸውን ተናግረዋል።

መንግስት ችግሮቹን ለመፍታት በአገር አቀፍ ደረጃ በተሽከርካሪዎች በካይ ጋዝ ልቀት ላይ ቁጥጥር ለማድረግ የሚያስችል መመሪያ ማውጣቱን አስታውቀዋል።  

ቢሮው መመሪያውን ተግባራዊ ለማድረግ ለባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብር ማካሄዱን ጠቅሰው ለተፈጻሚነቱ  የሚመለከታቸው አካላት  ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እና በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን በስፋት ጥቅም ላይ ለማዋል የተጀመሩ ተግባራት ከበካይ ጋዝ ልቀት ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያግዙ ሃላፊው ተናግረዋል።


 

'የፓርትነርሺፕ ፎር ሄልዝ ሲቲ ፕሮጀክት' ከፍተኛ አማካሪ ተፈሪ አበጋዝ በበኩላቸው፤ ከተሽከርካሪዎች የሚወጣው በካይ ጋዝ ጤናማ አካባቢ ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት ፈተና መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህም ከተሽከርካሪዎች የሚወጣውን የበካይ ጋዝ ልቀት ለመቆጣጠር መመሪያውን በፍጥነት መተግበር አስፈላጊ ነው ብለዋል።

የተሽከርካሪ የቴክኒክ ምርመራ ማህበር ምክትል ሰብሳቢ በሀይሉ ገረሱ ከበካይ ጋዝ ልቀት ጋር በተያያዘ የወጣው መመሪያ ውጤታማ እንዲሆን ማህበሩ የበኩሉን ሚና እንደሚጫወት አስታውቀዋል።

የጎህ ታክሲ ባለንብረቶች ሰብሳቢ ሰላማዊት ጌታቸው በበኩላቸው ተሽከርካሪዎች ከበካይ ጋዝ ልቀት ነፃ  እንዲሆኑ የሚከናወኑ ተግባራት የሚበረታቱ መሆናቸውን ተናግረዋል። 

ለአብነት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በስፋት እንዲገቡ መደረጉ እና የበካይ ጋዝ ልቀትን ለመቆጣጠር መመሪያ መውጣቱ የሚደገፍ ተግባር መሆኑን አንስተዋል። 

መንግሥትም ተሽከርካሪዎች ከበካይ ጋዝ ልቀት ነፃ እንዲሆኑ ለዘርፉ ተዋናዮች አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም