ቀጥታ፡

የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ ቀያቸው ተመልሰው እንዲኖሩ ለመቀበል ዝግጁ ነን

አዲስ አበባ፤ መስከረም 29/2018(ኢዜአ)፦ ከወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ ቀያቸው ተመልሰው ኑሯቸውን እንዲቀጥሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ከፍተኛ አመራሮች ገለጹ።

የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አሸተ ደምለው እና የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪና የሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ በሰጡት ማብራሪያ፤ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ከዞኑ የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱና ሰላማዊ ኑሯቸውን እንዲቀጥሉ እየተደረገ ነው ብለዋል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አሸተ ከዞኑ የተፈናቀሉና ያልተመለሱ ወገኖች ወደ ቀያቸው ተመልሰው ሰላማዊ ኑሯቸውን እንዲቀጥሉ እንደሚቀበሏቸው ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በወልቃይት ጠገዴ የሚኖሩ በርካታ የትግራይ ተወላጆች ሰላማዊ ህይወታቸውን እየመሩ እንደሚገኙ ጠቅሰው፤ የአማራና የትግራይ ህዝብ ለዘመናት አብረው የኖሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የሰሜኑ ጦርነት በተከሰተበት ወቅት ብዙዎች በኖሩበት አካባቢ እየኖሩ መሆኑን አስታውሰው፤ በወቅቱ ተደናግጠው ከሄዱት መካከል ደግሞ ወደ ዞኑ ተመልሰው ሰላማዊ ህይወት መምራት የጀመሩ መኖራቸውን ተናግረዋል።

ምክትል ዋና አስተዳዳሪው ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ በበኩላቸው እንደገለጹት ከዞኑ የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ አካባቢያቸው መመለስ አለባቸው።

በአካባቢው ሰላም ለመፍጠር አንድን ማህበረሰብ አፈናቅለህ አንዱን ማኖር የሚቻል አይመስለኝም ብለዋል።

ምክትል ዋና አስተዳዳሪው፤ የተፈናቃዮች ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ እልባት እንዲያገኝ በሁሉም በኩል ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግም አብራርተዋል።

መንግስት ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ለማድረግ በተከታታይ የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውንና ጥረቶች ሲያደርግ መቆየቱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም