ማህበረሰቡ በአዕምሮ ጤና አጠባበቅ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው በማድረግ የአዕምሮ ህመምን መከላከል ይገባል -ዶክተር መቅደስ ዳባ - ኢዜአ አማርኛ
ማህበረሰቡ በአዕምሮ ጤና አጠባበቅ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው በማድረግ የአዕምሮ ህመምን መከላከል ይገባል -ዶክተር መቅደስ ዳባ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 29/2018(ኢዜአ)፡- ማህበረሰቡ በአዕምሮ ጤና አጠባበቅ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው በማድረግ የአዕምሮ ህመምን መከላከል እንደሚገባ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ።
የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የአዕምሮ ጤና አጠባበቅ ላይ ያተኮረ የጥናትና ምርምር ኮንፈረንስ እያካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ እንደገለጹት የማህበረሰቡን ጤና በተሻለ መልኩ መጠበቅ የሚያስችል የጤና ፖሊሲ እየተተገበረ ይገኛል።
በተለይም ለአዕምሮ ጤና እክል ልዩ ትኩረት በመስጠት በጥናት አስደግፎ ችግሩን ቀድሞ ለመከላከል የሚያስችሉ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።
የአዕምሮ ጤና መታወክ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ ትልቅ መሆኑን አንስተው በዘርፉ የተከናወኑ ጥናቶችን መሰረት በማድረግ ማህበረሰቡ በአዕምሮ ጤና ዙሪያ ግንዛቤው እንዲያድግ ሊሰራ እንደሚገባም ተናግረዋል።
በዚህም ረገድ ባለድርሻ አካላት ማህበረሰቡ በአዕምሮ ጤና አጠባበቅ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው በማድረግ ከአዕምሮ ጤና ጋር የሚያያዙ ችግሮችን የመከላከል ሚናቸውን ማጠናከር አለባቸው ብለዋል።
የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ፕሮፌሰር ነፃነት ወርቅነህ በበኩላቸው በክልሉ የተለያዩ በሽታዎችን ለመከላከል በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አንስተዋል።
የአዕምሮ ጤና ችግር አንዱ መሆኑን አውስተው የአዕምሮ ጤና መታወክ በህክምና የሚድን ቢሆንም በማህበረሰቡ ውስጥ ባለ የተሳሳተ ግንዛቤ የችግሩ ተጠቂዎች ለተለያየ ጉዳት ይዳረጋሉ ብለዋል።
በቀጣይም በጤና ዙሪያ የሚሰሩ አካላት ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር ማህበረሰቡ በአዕምሮ ጤና ዙሪያ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው መረባረብ እንደሚገባም አመልክተዋል።
በመድረኩ ላይ የውይይት መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት ፕሮፌሰር ሙስጠፋ አልአብሲ፣ የአዕምሮ ጤና ችግሮች ውስብስብና ሁለንተናዊ የጤና ችግር የሚያስከትሉ ናቸው ብለዋል።
በማህበረሰቡ ዘንድ ባለው የግንዛቤ እጥረት በአዕምሮ በሽታ የተያዙ ወገኖች እንዲገለሉ በማድረግ የበለጠ ችግሩ እንዲባባስ የሚያደርግ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በማህበረሰቡ ዘንድ ያለውን ግንዛቤ በማሳደግ ችግሩን ቀድሞ መከላከል እና ችግሩ ሲያጋጥምም በሳይንሳዊ መንገድ ማከም ላይ በትብብር መስራት እንደሚገባም አስረድተዋል።