በአማራ ክልል የፍርድ ቤቶችን አገልግሎት ፈጣን፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለበት ለማድረግ የሚያስችሉ አሰራሮች ተግባራዊ እየተደረጉ ነው- ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የፍርድ ቤቶችን አገልግሎት ፈጣን፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለበት ለማድረግ የሚያስችሉ አሰራሮች ተግባራዊ እየተደረጉ ነው- ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ

ባሕር ዳር፤ መስከረም 29/2018(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል የፍርድ ቤቶችን አገልግሎት ፈጣን፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለበት ለማድረግ የሚያስችሉ አሰራሮች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።
የአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች የዳኞች ጉባዔ የማጠቃለያ ፕሮግራም የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና ሌሎችም የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ተካሂዷል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፤ በክልሉ የላቀ የፍትህ አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ስራ በተቀናጀ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
የፍርድ ቤቶችን ገለልተኛነትና ነፃነታቸውን በማረጋገጥ በሕዝብ ይበልጥ አመኔታ እንዲኖራቸው ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል።
በመሆኑም የፍርድ ቤቶችን አገልግሎት ፈጣን፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለበት ለማድረግ የሚያስችሉ አሰራሮች በስፋት ተግባራዊ እየተደረጉ ይገኛሉ ብለዋል።
የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኘሬዚዳንት አለም አንተ አግደው፤ የፍርድ ቤቶችን አገልግሎት አሰጣጥ በብቁ የሰው ሃይልና በቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ ፍትሃዊ፣ ፈጣን፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለበት የማድረግ ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች በማክበርና በማስከበር ረገድም ፍርድ ቤቶች ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው በማንሳት የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ስራ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ተናግረዋል።
የጉባዔው ዓላማም የዳኞችን የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ጥረትና የመሪነት ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ለማስቻል መሆኑን አንስተው ፤ በጉባዔው የዳኝነት ሪፎርም፣ የክልሉ የ25 ዓመት አሻጋሪ የልማት ፋኖተ ካርታና የ5 ዓመት ስትራቴጅክ ዕቅድ ላይም ምክክር ተደርጓል ብለዋል።
የባህላዊ ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ፣ የአመራር ጥበብ፣ የሙያ ሰነ ምግባር ግንባታ፣ የሙስና መከላከል ስትራቴጂን መመልከቱንም ጠቁመዋል።
ከመስከረም 20/2018 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የሰነበተው የክልሉ ፍርድ ቤቶች የዳኞች ጉባዔ ለዘርፉ ውጤታማነት የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት እውቅና በመስጠት ተጠናቋል።