ቀጥታ፡

ፕሬዝዳንቱ ለሁለቱ ምክር ቤቶች ያቀረቡት ንግግር የፌደራል መንግስት ዓመታዊ ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎችን ያመላከተ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 29/2018 (ኢዜአ)፡- በፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ለሁለቱ ምክር ቤቶች የቀረበው የመክፈቻ ንግግር የፌደራል መንግሥትን የ2018 ዋና ዋና ሀገራዊ የልማት ዕቅዶችና የትኩረት አቅጣጫዎችን ያመላከተ መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ገለጹ።

6ኛው ዙር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ5ኛ ዓመት የስራ ዘመን አንደኛ መደበኛ ስብሰባ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ለሁለቱ ምክር ቤቶች ያደረጉትን የመክፈቻ ንግግር ላይ የቀረበን የድጋፍ ሞሽን አዳምጧል።


 

ምክር ቤቱ በመጀመሪያ አጀንዳው በሐምሌ ወር 2017 ዓ.ም የተካሄደውን የምክር ቤቱ 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ አስቸኳይ ስብሰባ ቃለ-ጉባኤ መርምሮ አጽድቋል።

በመቀጠልም ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ መስከረም 26/2018 ዓ.ም ለህዝብ ተወካዮችና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ የመክፈቻ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር ላይ የቀረበውን የድጋፍ ሞሽን አዳምጧል።

የድጋፍ ሞሽኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ለምክር ቤቱ አባላት በጽሁፍ አቅርበዋል፡፡

በዚህም በሕገ-መንግስቱ፣ በምክር ቤቱ የአባላት የሥነ-ምግባርና የአሠራር ደንብ መሠረት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ መስከረም 26/2018 ዓ.ም የመክፈቻ ንግግር ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

በሁለቱም ምክር ቤቶች የጋራ ስበሰባ ያቀረቡት የመክፈቻ ንግግር የፌደራል መንግስት ዓመታዊ የልማት ዕቅድ ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎችን የተመላከቱበት መሆኑን አንስተዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አብርሃም ዓለማየሁ (ዶ/ር)÷ በሁለቱ ምክር ቤቶች መክፈቻ ላይ መንግስት በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ መስኮች የልማት ስኬትን ማስቀጠል የሚያስችሉ አጀንዳዎችን ይፋ ማድረጉን ገልጸዋል።

የሀገርን ክብርና ከፍታ የሚመጥኑ የዲፕሎማሲ፣ የትምህርት፣ ጤናና የኢኮኖሚ መሠረተ ልማቶችን በመገንባት ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና የሚያሸጋግሩ ዕቅዶች መካተታቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም