ከአዲስ አበባ በተጨማሪ የክልል ከተሞችን ዓለም አቀፍ የኮንፍረንስ ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ ትኩረት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
ከአዲስ አበባ በተጨማሪ የክልል ከተሞችን ዓለም አቀፍ የኮንፍረንስ ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ ትኩረት ተደርጓል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 29/2018 (ኢዜአ)፡- ከአዲስ አበባ በተጨማሪ የክልል ከተሞችን ዓለም አቀፍ የኮንፍረንስ ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ ትኩረት መሰጠቱን የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አምስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን የጋራ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ መንግሥት ባለፉት ዓመታት የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ ትኩረት በመስጠት አዝጋሚ የነበረውን ጉዞ ወደ ጉልህ የእድገት አንቀሳቃሽ ሞተር መለወጥ መቻሉን ተናግረዋል።
ይህን ተሞክሮ በማስፋት በዚህ በጀት ዓመት የተዋበች ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚያስችሉ የቱሪዝም መዳረሻ የማብዛት ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላል ብለዋል።
ነባሮቹ የቱሪዝም መስሕቦቻችን ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ በማልማት ለጎብኚዎች ምቹ እንዲሆኑ ይደረጋል ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ።
በቀጣይም በዘርፉ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ እንደሚሠራ ተናግረዋል።
የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ ለኢዜአ እንደገለጹት ኮንፈረንስ ቱሪዝም ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ከሚኖረው ቀጥተኛ ፋይዳ በተጨማሪ ኢትዮጵያን ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
ሚኒስትር ዴኤታው እንዳስታወቁት፣ ኢትዮጵያ ባለፈው በጀት ዓመት ከ150 በላይ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን በማዘጋጀት በሀገሪቱ ታሪክ ከፍተኛውን ቁጥር አስመዝግባለች።
ይህ ቁጥር ከአብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት ዓመታዊ የኮንፈረንስ አዘጋጅነት እጅግ የላቀ መሆኑን አብራርተዋል።
ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የስብሰባ ማዕከል አለመኖር ፈታኝ እንደነበር ያስታወሱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ የአዲስ ኮንቬንሽናል ማዕከል እውን መሆን ትልቅ ለውጥ በማምጣት ለኮንፈረንስ ቱሪዝም መበራከት ወሳኝ ሚና ተጫውቷል ብለዋል።
የአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ግንባታ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በርካታ መዳረሻዎች እንዲሁም በዘርፉ የሚሰጠውን አገልግሎት ቀልጣፋ ማድረግ መቻሉ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ተናግረዋል።
መንግሥት የኮንፈረንስ ቱሪዝም በአዲስ አበባ ሳይወሰን በክልል ከተሞች እንዲስፋፋ በማድረግ የዘርፉን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማሳደግ የሚያስችል ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
መቀሌ፣ ባህር ዳር፣ አዳማ እና ሀዋሳ የኮንፈረንስ ቱሪዝምን ለማስፋፋት ትኩረት ከተሰጣቸው ከተሞች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው ይህ ጥረት የሀገሪቱን የቱሪዝም አቅም የበለጠ ለማሳደግ እና ኢትዮጵያን የዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ማዕከል ለማድረግ የተያዘውን ግብ ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
ሚኒስቴር ዴኤታው በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ባለሀብቶች ለዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ቱሪዝም ወሳኝ በሆነ ተግባራት ላይ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።