ቀጥታ፡

የሳይበር ደህንነት ወር “የሳይበር ደህንነት - የዲጂታል ኢትዮጵያ መሰረት” በሚል መሪ ሀሳብ ከጥቅምት 1 ጀምሮ ይከበራል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 29/2018(ኢዜአ)፦ ስድስተኛው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር “የሳይበር ደህንነት - የዲጂታል ኢትዮጵያ መሰረት” በሚል መሪ ሀሳብ ከጥቅምት 1 እስከ 30/2018 ዓ.ም እንደሚከበር የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር አስታወቀ።

የሳይበር ደህንነት ወር አከባበርን በማስመልከት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግሥት ሃሚድ በሰጡት መግለጫ፥ የሳይበር ጥቃት በዓለም አቀፍ ደረጃ በቁጥርም ሆነ በአይነት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ይገኛል ብለዋል። 

የሳይበር ደህንነት ወር መከበር ዋነኛ ዓላማው የዜጎችንና የተቋማትን የሳይበር ደህንነት ግንዛቤ የሚያጎለብቱ የንቅናቄ መድረኮችን በማዘጋጀት ሀገራዊ የሳይበር ደህንነት የመከላከል አቅምን ለማሳደግ ነው ብለዋል።

“የሳይበር ደህንነት - የዲጂታል ኢትዮጵያ መሰረት” በሚል መሪ ሀሳብ የሚከበረው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህነንት ወር ሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግም ተናግረዋል።

የመጀመሪያው የሃሰተኛ መረጃ ዝግጅት፣ ቁጥጥርና ስርጭትን ለመቆጣጠር እና ለመከላከል ያለመ ንቅናቄ መሆኑን ገልጸዋል።

በሁለተኛ ደረጃ በዲጂታላይዜሽን ደህንነት ጉዞ የተቋማትን የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነት ለመቀነስ የሚያስችል ንቅናቄ መሆኑን ተናግረዋል። 

6ኛው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር አስፈላጊነትም ተቋማት በሰፊዉ ወደ ዲጂታላይዜሽን እየገቡ በመሆኑ ከወዲሁ የሳይበር ደህንነት ዝግጁነታቸዉን መጨመር እንዲችሉ ነው ብለዋል። 

የሳይበር ደህንነት ወር የመክፈቻ መርሃ ግብር ጥቅምት 1 ቀን 2018 እንደሚካሄድ በማንሳት ወሩን ሙሉ በተለያዩ ከተሞች የህብረተሰቡን ንቃተ ህሊና የሚያሳድጉ መርሃ ግብሮች እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም