የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት መምህራን ግንባር ቀደም ሚናቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል--የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር - ኢዜአ አማርኛ
የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት መምህራን ግንባር ቀደም ሚናቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል--የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር
አዳማ፤ መስከረም 29/2018(ኢዜአ)፡- የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት መምህራን ግንባር ቀደም ሚናቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ገለጸ።
ከሁሉም ክልሎች የተወጣጡ የመምህራን ተወካዮች የተሳተፉበት 38ኛው የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር መደበኛ ምክር ቤት ጉባኤ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የኢትዮጰያ መምህራን ማህበር ፕሬዚደንት ዮሐንስ በንቲ (ዶ/ር) በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት የትምህርት ጥራት እንዲረጋገጥ ማህበሩ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
በእስካሁኑ ሂደትም የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ የምርምር ሥራዎችን በማከናወን የምርምር ውጤቶቹ ጥራትን ለማስጠበቅ ግብዓት እንዲሆኑ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይም የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ መምህራን ግንባር ቀደም ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባና ለዚህም ማህበሩ ያግዛል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት ደምመላሽ መንግስቱ (ዶ/ር) በበኩላቸው በተቋማቱ የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ ዋነኛ አጀንዳ ሆኖ እየተሰራበት ይገኛል።
የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ ረገድ መምህራን ሙያዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ ከማገዝ ጀምሮ ዘርፉን በምርምር መደገፍ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይ አዲሱን የትምህርት ፖሊሲ ወደመሬት ለማውረድና የሚፈለገው የትምህርት ጥራት እንዲረጋገጥ መምህራንና የዘርፉ ምሁራን በምርምር እንዲያግዙ ማህበሩ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ቶላ በሪሶ (ዶ/ር) እንደገለጹት በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ መምህራንን የማብቃት ሥራ በተከታታይ እየተሰራ ይገኛል።
በተለይ የትምህርት ጥራትን ከታችኛው የትምህርት እርከን ጀምሮ ለማረጋገጥ በቅድመ መደበኛ ትምህርት ላይ ባለፉት ሦስት ዓመታት ውጤታማ ስራ ተሰርቷል ብለዋል።
በዚህም በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች 17 ሺህ 520 ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ለመቀበል መቻሉን ነው የገለጹት።
በተመሳሳይ ከ1 እስከ 5ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች የማንበብ፣ የመጻፍና የማስላት ችግሮችን ለመፍታት 57 ሺህ የቋንቋና የሒሳብ መምህራን ስልጠና ወስደው ወደ ስራ መግባታቸውን ተናግረዋል።