የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ካለው ጉልህ ጠቀሜታ አንጻር የሁሉም ቀዳሚ አጀንዳ ሆኖ መቀጠል አለበት -ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ካለው ጉልህ ጠቀሜታ አንጻር የሁሉም ቀዳሚ አጀንዳ ሆኖ መቀጠል አለበት -ምሁራን

ቦንጋ፤ መስከረም 29/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ሀገራዊ የብልጽግና ጉዞን ለማሳለጥና ሉአላዊነትን ለማስጠበቅ ካለው ጉልህ ጠቀሜታ አንጻር የሁሉም ቀዳሚ አጀንዳ ሆኖ መቀጠል አለበት ሲሉ ምሁራን ገለጹ።
የባህር በር ጥያቄ ለኢትዮጵያ የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ሀገራዊ ጥቅምን ለማስከበር በአንድነት መቆም እንደሚገባም ምሁራኑ ተናግረዋል።
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በሁለቱ ምክር ቤቶች የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄዋን በሰላማዊ መንገድ ማቅረቧን ተከትሎ ጥያቄው በዓለም አቀፍ ደረጃ ቅቡልነት እያገኘ መምጣቱንና ይህን ለማሳካት በተያዘው ዓመትም መንግስት አበክሮ እንደሚሰራ መናገራቸው የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎት ያለውን ሀገራዊ ፋይዳ በማስመልከት ኢዜአ ያነጋገራቸው የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና የታሪክ ምሁራን መንግስት የባህር በር ለማግኘት እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታና የሚደገፍ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ሀገራዊ የብልጽግና ጉዞን ለማሳለጥና ሉአላዊነትን ለማስጠበቅ ካለው የጎላ ጠቀሜታ አንጻር የሁሉም ቀዳሚ አጀንዳ ሆኖ መቀጠል እንዳለበትም ተናግረዋል።
በቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ያሬድ አያሌው፣ ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት የባህር በር ባለቤት እንደነበረች አስታውስዋል።
ይሁን እንጂ ሸፍጥ በተሞላበትና የህዝብ ይሁኝታ በሌለበት የባህር በሯን እንድታጣ መደረጉንና ይህም ለዘመናት በኢኮኖሚ እድገቷ ላይ ከፍተኛ ጫና ሲያሳድር መቆየቱን ገልፀዋል።
በምስራቅ አፍሪካ ከ130 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላት ሀገር ያለባህር በር መኖሯ ሉአላዊነቷን ስጋት ውስጥ ከመክተት ባለፈ በቀጣናው ሰላም ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንዳለውም ተናግረዋል።
የባህር በር ጉዳይ እንደነውር መታየቱ ቀርቶ አሁን ላይ ጥያቄው በመንግስት በይፋ መቅረቡ የሚደገፍ ነው ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር ያሬድ፣ የባህር በር ሀገራዊ የብልፅግና ጉዞ ለማሳለጥና ሉአላዊነቷን ለማስጠበቅ ካለው አስፈላጊነት አንፃር የሁሉም ቀዳሚ አጀንዳ ሆኖ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በዓለም አቀፍ ህጎችም ይሁን በታሪክ ተገቢነት እንዳለው ገልጸው፣ ጥያቄው እንዲሳካ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
“የተለየያ አመለካከትና ፍላጎት ቢኖረንም እንኳን የሀገር ጥቅም ለማስከበር በአንድነት መቆም ይገባናል” ብለዋል።
ጥያቄው ከዳር እስኪደርስ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያሳየነውን አንድነትና ትብብር በባህር በርም መድገም ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት መሆን ከራሷ ባለፈ ለአካባቢው ሰላምና የጋራ ልማት ትልቅ አበርክቶ እንዳለው የተናገሩት ደግሞ የታሪክ ምሁሩ አሸብር ሙላቱ ናቸው።
ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ የቀይ ባህር ባለቤትና በቀጣናው ገናና መንግስት ያላት ሀገር እንደነበረች አስታውሰው፣ የባህር በር ጥያቄ ለኢትዮጵያ የቅንጦት ሳይሆን የህልውናና የደህንነት ጉዳይ ነው ብለዋል።
መንግስት ኢትዮጵያ በቀጣናው የነበራትን ይህን ሀያልነት ለመመለስ የባህር በር እንድታገኝ የጀመረው መንገድና የያዘው አቋም የሚበረታታ መሆኑን ገልጸው፤ የኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎት እውነትና ታሪካዊ መሰረት እንዳለው ተናግረዋል።
የባህር በር ጥያቄው ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ መንግስት የጀመረውን የዲፕሎማሲ መንገድ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸው፣ ኢትዮጵያዊያን በሕዳሴው ግድብ ያሳየነውን ትብብርና አንድነት በባህር በር ማጠናከር ይገባናል ሲሉም ተናግረዋል።