ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የአፍሪካን የኢኮኖሚ ታሪክ የመቀየር ልዩ እድል ይዞ መጥቷል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የአፍሪካን የኢኮኖሚ ታሪክ የመቀየር ልዩ እድል ይዞ መጥቷል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ መስከረም 29/2018(ኢዜአ)፦ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የአፍሪካን የኢኮኖሚ ታሪክ የመቀየር ልዩ እድል ይዞ መምጣቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ዛሬ በኬንያ ናይሮቢ “ዲጂታላይዜሽንን ለቀጠናዊ የእሴት ሰንሰለት መጎልበት በመጠቀም ለዘላቂ እና አካታች እድገት ማዋል” በሚል ጭብጥ በተካሄደው 24ኛው የCOMESA መሪዎች ጉባኤ ላይ ተሳትፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት በጉባኤው ላይ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የአፍሪካን የኢኮኖሚ ታሪክ የመቀየር ልዩ እድል ይዞ መምጣቱን አፅንኦት ሰጥተው ማንሳታቸውን ገልጸዋል።
እንደ አኅጉር የየሀገራቶችን ጥረቶች ለማጣመር እና ቀጠናዊ ትስስሮችን ለማፋጠን ክሂሎቱ እና መሠረቱ አለን ብለዋል።
በኢትዮጵያ ዲጂታል ክሂሎትን ለማበልጸግ እና አስፈላጊ መሠረተ ልማት ለመገንባት ጥሩ ርምጃዎች ተራምደናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጋራ ዲጂታል ነጋችንን ለማሳደግ በትብብር ለመሥራት ዝግጁ ነን ሲሉም ተናግረዋል።