ቀጥታ፡

በወጣቶችና አፍላ ወጣቶች ላይ የሚከሰቱ የጤና እክሎችን መግታት የሚያስችል የጤና አገልግሎትን ይበልጥ ለማስፋፋት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 29/2018(ኢዜአ)፦ በወጣቶችና አፍላ ወጣቶች ላይ የሚከሰቱ የጤና እክሎችን መግታት የሚያስችል የጤና አገልግሎትን ይበልጥ ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ገለጹ።

6ኛው ሀገራዊ የአፍላ ወጣቶች እና ወጣቶች ጤና ጉባኤ በአዲስ አበባ በሐምሊን ፊስቱላ ሆስፒታል ተካሂዷል።


 

የጤና ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በመድረኩ መንግሥት የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ባከናወናቸው ተግባራት አበረታች ውጤት ማምጣት መቻሉን ተናግረዋል።

በተለይም ባለፉት የለውጥ ዓመታት በወጣቶችና አፍላ ወጣቶች ላይ ትኩረት ያደረገ የጤና አጠባበቅ ሥርዓት መዘርጋት ዋነኛው የሥራ መስክ መሆኑን አብራርተዋል።

የወጣቶች ያለ ዕድሜ ጋብቻ መፈጸም ለፊስቱላና ለመሰል ከባድ የጤና ጉዳቶች የመጋለጥ እድል የሚጨምር ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡

ጉባኤው ለወጣቶች ዘርፍ ከፍተኛ ጥቅምና ትርጉም ያለው መሆኑን ገልጸው፤ በወጣቶች ዙሪያ በሚከናወኑ ተግባራት የባለድርሻ አካላትን ቅንጅታዊ አሠራር ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም፣ በወጣቶች የጤናና መሰል አገልግሎቶች ላይ ያሉ ውስንነቶችን ለመለየትና የመፍትሔ አቅጣጫ ለመቀየስ ቁልፍ ሚና እንደሚኖረው አስረድተዋል።

በጤና ሚኒስቴር የአፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ጤና ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ዶክተር ገመቹ አቤ በበኩላቸው፤ መንግስት የወጣቶችን ሁሉን አቀፍ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እያከናወነ ያለው ተግባር የሚበረታታ ነው ብለዋል።


 

በተለይም ጤንነቱ የተጠበቀ አምራች ዜጋን በመፍጠር ረገድ የሚከናወኑ ተግባራት ወጣቶች በአገር ሁለንተናዊ እድገት ላይ ያላቸውን ተሳትፎ እንዲያጠናክሩ እድል ፈጥሯል  ብለዋል።

በበጎ ፈቃድ በሚሰጥ የጤና አገልግሎት ወጣቶች እንዲሳተፉ መደረጉ የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ አይነተኛ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

የፊስቱላ ኢትዮጰያ ሆስፒታል የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር መንግስቱ አስናቀ ሆስፒታሉ ያለ እድሜ ጋብቻን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ለጤና እክል ለተዳረጉ ሴቶች የተሟላ ህክምና በመስጠት ላይ ይገኛል ብለዋል።


 

በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባን ጨምሮ በአምስት የአገሪቱ አካባቢዎች ማዕከላትን በማቋቋም ተደራሽነቱን ለማስፋት ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሆስፒታሉ ከሚሰጠው ህክምና ባሻገር መከላከልን መሰረት ያደረገ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ጠቁመው ይህም እንደ አገር ችግሩን ለመቅረፍ አይነተኛ ሚና አለው ብለዋል።

ጉባኤው "አንድነትን ለተግባራዊ እርምጃ የአፍላ ወጣትነት እርግዝናን ለማስቆም እንተባበር" በሚል መሪ ሃሳብ ነው የተካሄደው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም