በድሬዳዋ ግንባታቸው የተጠናቀቁ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ተመርቀው ስራ ጀመሩ - ኢዜአ አማርኛ
በድሬዳዋ ግንባታቸው የተጠናቀቁ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ተመርቀው ስራ ጀመሩ
ድሬዳዋ፤መስከረም 29/2018 (ኢዜአ)፦ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በድሬዳዋ ግንባታቸው የተጠናቀቁ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎችን መርቀው ስራ አስጀመሩ።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሐር እና ሌሎችም ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ከተመረቁት መካከል በ350 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው ሂልዋ የማዳበሪያ ከረጢት ማምረቻ እና የዱቄት ፋብሪካዎች ይገኙበታል።
በዚሁ መርሃ ግብር ላይ ንግግር ያደረጉት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል፤ የኢንዱስትሪ ዘርፉን የማስፋፋትና ምርታማነትን የማሳደግ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፉት ሶስት ዓመታት እንደ ሀገር በተካሄደው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን አስታውሰው ዘርፉን የማስፋትና ምርታማነት የማሳደግ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
መንግስት ባደረገው የተቀናጀ ድጋፍና ቁርጠኝነት አዳዲስ ፋብሪካዎችን ወደ ስራ በማስገባት እና የነባሮቹን የማምረት አቅም በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር ማስቻሉን አንስተዋል ።
ፋብሪካዎቹ ገቢ ምርቶችን በመተካት፣ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን በጥራትና በብዛት በማምረት አበረታች ውጤቶች እያስመዘገቡ ይገኛሉ ብለዋል።
በድሬዳዋ በዘርፉ እየተካሄደ የሚገኙ የንቅናቄ ተግባራት በአርአያነት የሚጠቀሱ መሆኑን አንስተው፤ ዛሬ ተመርቀው ወደ ስራ እየገቡ የሚገኙት ፋብሪካዎች የዚሁ መገለጫ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር፤ ድሬዳዋ ያላትን መሠረተ ልማት በመጠቀም የንግድና የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም በለውጡ ዓመታት እና በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ እየተመዘገበ የሚገኘው ውጤትና ለወጣቶች እየተፈጠረ የሚገኘው የስራ እድል ለአብነት ይጠቀሳል ብለዋል።
እየተመረቁ ከሚገኙት አዳዲስ ፋብሪካዎች በተጨማሪ በአስተዳደሩ በስራ ላይ የሚገኙ 69 ፋብሪካዎች ተኪ ምርቶችን በማምረት የውጭ ምንዛሪ እያስገኙ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በድሬዳዋ የሚገኙ ፋብሪካዎች ምርትና ምርታማነታቸው እንዲጨምር እያገዘ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ ሀርቢ ቡህ ናቸው።
በዛሬው እለት ተመርቀው ለአገልግሎት ከበቁ ፋብሪካዎች መካከል የዱቄት፣ የሚስማር፣ የህክምና ቁሶች ማምረቻ፣ የወተት ማቀነባበሪያ፣ የምግብ ጨው እና የሜታል ክራፍት እና ሌሎችም ይገኙበታል።