የመቱ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ የምርምር ስራዎችን በማፍለቅ የአካባቢውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ እያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመቱ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ የምርምር ስራዎችን በማፍለቅ የአካባቢውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ እያደረገ ነው

መቱ ፤መስከረም 29/2018(ኢዜአ) :- የመቱ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ የምርምር ስራዎችን በማፍለቅ የአካባቢውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ገለጸ።
ዩኒቨርሲቲው ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያካሄዳቸው የምርምር ውጤቶች ላይ ያተኮረ የባለድርሻ አካላት ውይይት መካሄዱ ይታወሳል።
ዩኒቨርሲቲው ያካሄዳቸው የምርምር ውጤቶች የግብርናውን ዘርፍ ውጤታማ የሚያደርጉ በተለይም የሆርቲካልቸር፣ የእንስሳት ሀብት ልማትና የምርጥ ዘር ብዜት ላይ ያተኮሩ መሆናቸው ተገልጿል።
የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ፣ የምርምርና ማሕበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት በድሉ ተካ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው በግብርና፣ በጤናና በትምህርት ዘርፍ ያካሄዳቸውን የምርምር ውጤቶችን ለተጠቃሚ እያስተዋወቀ ይገኛል።
በተለይ በግብርናው ዘርፍ የፍራፍሬና የቡና ልማት ላይ እንዲሁም በእንስሳት ሀብት ልማት ደግሞ የወተት ላሞች ዝርያን በማሻሻል የወተት ምርትን ማሳደግ የሚያስቸሉ የምርምር ውጤቶች ይፋ ማድረጉን ተናግረዋል።
በተፈጥሮ ሀብት አጠባበቅ ዘርፍም ብዝሀ ህይወት እንዲጠበቅ ማህበረሰቡን ያሳተፉ የምርምር ስራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በጤና ዘርፍ ባሕላዊ መድኃኒቶችን በሳይንሳዊ መንገድ መጠቀም የሚያስችሉ አቅሞችን ለመፍጠር ጥናትና ምርምር ስራዎች እየተደረጉ መሆኑንም ገልጸዋል።
በተለይ በእጽዋት ላይ የተደረጉ የምርምር ስራዎች የአረንጓዴ አሻራና የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብርን ስኬታማነት በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያግዙ መሆናቸውን አክለዋል።
በሰብል ልማትና እንስሳት እርባታም በተለይ ምርታማነትን ማሳደግ ላይ ያተኮሩ የምርጥ ዘር ግኝትና ብዜት ላይ ለሚሰራው ስራ አጋዠ ነውም ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው የምርምር ውጤቶቹን በማስፋት በኢሉአባቦርና በቡኖ በደሌ ዞኖች እያሰራጨ እንደሚገኝ አመልክተው በቀጣይም የጥናትና ምርምር ስራዎቹን ከማጠናከረ ባለፈ በሰው ኃይል ልማት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑም ተናግረዋል።