በህብረ ብሄራዊ አንድነት የህዳሴ ግድብን እንዳሳካን ሁሉ የባህር በር ባለቤት ለመሆን ልንዘጋጅ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በህብረ ብሄራዊ አንድነት የህዳሴ ግድብን እንዳሳካን ሁሉ የባህር በር ባለቤት ለመሆን ልንዘጋጅ ይገባል
ሀዋሳ ፤ መስከረም 29/2018(ኢዜአ)፡-በህብረ ብሄራዊ አንድነትና በጽናት የህዳሴ ግድብን እንዳሳካን ሁሉ የባህር በር ባለቤት በመሆን ለመድገም ልንዘጋጅ ይገባል ሲሉ የሲዳማ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ተናገሩ።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሲዳማ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ በለጠ ስጌቦ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአንድነታችን ምልክት ነው ብለዋል ።
የግድቡ ግንባታ ለዘመናት ሲነሳ የነበረ የህዝብንና ሀገርን የመልማት ቁጭት ለማሳካት ያለልዩነት በመቆም ያሳካነው ድል ነው ብለዋል ።
እንደ ሰብሳቢው ገለፃ የህዳሴውን ግድብ በህብረት እንዳጠናቀቅን ሁሉ የባህር በር ፍላጎታችንን እውን ለማድረግም በአንድነት ልንቆም ይገባል።
ለግድቡ ግንባታም ከሊቅ እስከ ደቂቅ መላው ዜጋ እንዲሁም ፓርቲዎች አቋማቸውን አንድ በማድረግ አባሎቻቸውን አስተባብረው ድጋፍ ሲያደርጉ እንደነበር አስታውሰዋል።
የህዳሴ ግድቡ ልክ ኢትዮጵያዊነት ነው ያሉት አቶ በለጠ ይህን ለማስከበር ያለ ልዩነት የተደረገው ጥረት ለስኬት በቅቷል ብለዋል።
የግድቡ መጠናቀቅ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም በዘላቂነት ማስከበር መሆኑን ያነሱት አቶ በለጠ ይህም የሀገሪቱን የመልማት ፍላጎትን ከማሳካት ባለፈ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያለውን ቀውስ ያረጋጋ መሆኑንም አመልክተዋል።
አባይ ትርጉሙ ብዙ ነው የሚሉት አቶ በለጠ የኃይል ፍላጎቶችን በመመለስ በስራ ዕድል ፈጠራና ሀገራዊ ገቢን በማሳደግ እንዲሁም የውስጥ አንድነትን ከማጠናከር አንጻርም ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል።
የህዳሴው ግድብ መጠናቀቅ በጋራ ከቆምን የማናሳካው ጉዳይ እንደማይኖር በተግባር ያሳየንበት የትውልዱ ኩራት ነው ሲሉም ገልጸዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ የሀገሪቱን ዕድገትና ብሔራዊ ጥቅምን ያስከበረ የሰለጠነ ፖለቲካዊ አካሄድን ተግባራዊ ለማድረግ አበክሮ እንደሚሰራም ተናግረዋል።